Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ማርቆስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢየሱስ አራት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
( ማቴ. 15፥32-39 )

1 በዚያን ሰሞን እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ የሚበሉትም አልነበራቸውም፤ ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤

2 “እነዚህ ሰዎች እነሆ፥ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ቈይተዋል፤ ምንም የሚበሉት ምግብ ስለሌላቸው እራራላቸዋለሁ፤

3 እንዲሁ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይደክማሉ፤ እንዲያውም ከእነርሱ አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ናቸው።”

4 ደቀ መዛሙርቱም፦ “ታዲያ፥ በዚህ በረሓ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚበቃ እንጀራ ማግኘት ማን ይችላል?” ሲሉ መለሱለት።

5 ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ሰባት እንጀራ አለን፤” አሉት።

6 እርሱም በመሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ይዞ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አቀረቡ።

7 ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎችም ነበሩአቸው፤ ስለ ዓሣዎቹም እግዚአብሔርን ካመሰገነ በኋላ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ።

8 ሰዎቹም ሁሉ በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቊርስራሽ ሰብስበው ሰባት ትላልቅ መሶብ ሙሉ አነሡ።

9 የተመገቡት ሰዎች አራት ሺህ ያኽል ነበሩ፤ ኢየሱስ እነርሱን አሰናበታቸው።

10 ከዚያ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ሆኖ ወደ ዳልማኑታ አውራጃ ሄደ።


ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ
( ማቴ. 16፥1-4 )

11 ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጡና ከእርሱ ጋር መከራከር ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም አስበው ከሰማይ አንድ ተአምር እንዲያሳያቸው ጠየቁት።

12 ኢየሱስ በመንፈሱ በመቃተት፦ “የዚህ ዘመን ትውልድ ተአምር እንዲደረግለት ስለምን ይፈልጋል? በእውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ተአምር አይደረግለትም!” አላቸው።

13 ትቶአቸውም እንደገና በጀልባ ሆኖ ወደ ማዶ ተሻገረ።


የፈሪሳውያንና የሄሮድስ እርሾ
( ማቴ. 16፥5-12 )

14 ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም።

15 ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው።

16 እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።

17 ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን?

18 ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም?

19 ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት።

20 “እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት።

21 እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው።


ኢየሱስ በቤተ ሳይዳ አንድ ዐይነ ስውር መፈወሱ

22 ወደ ቤተ ሳይዳም በደረሱ ጊዜ ሰዎች አንዱን ዕውር ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት።

23 እርሱም ማየት የተሳነውን ሰው እጅ ይዞ እየመራ ከመንደር ወደ ውጪ አወጣው፤ በሰውየውም ዐይኖች ላይ ምራቁን እንትፍ ብሎ እጁን ጫነበትና “አንዳች ነገር ታያለህን?” ሲል ጠየቀው።

24 ዐይነ ስውሩም ቀና ብሎ፥ “አዎ ሰዎች ይታዩኛል፤ ግን እንደሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ፤” አለ።

25 እንደገናም ኢየሱስ በሰውየው ዐይኖች ላይ እጁን ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው ትኲር ብሎ አየ፤ ድኖም ሁሉን ነገር አጥርቶ ማየት ጀመረ።

26 ከዚያም በኋላ ኢየሱስ “ወደ መንደሩ አትግባ፤” ብሎ ወደ ቤቱ እንዲሄድ አሰናበተው።


ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ
( ማቴ. 16፥13-20 ፤ ሉቃ. 9፥18-21 )

27 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፊልጶስ ቂሳርያ በሚባለው ክፍለ ሀገር አካባቢ ወዳሉት መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ኢየሱስ፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።

28 እነርሱም፦ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ሌሎች ኤልያስ ነው፤ ሌሎችም ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል፤” ሲሉ መለሱለት።

29 “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ “አንተ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት።

30 ኢየሱስም፦ “ስለ እኔ ለማንም እንዳትናገሩ፤” ብሎ አስጠነቀቃቸው።


ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተናገረ
( ማቴ. 16፥21-28 ፤ ሉቃ. 9፥22-27 )

31 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል ማስተማር ጀመረ፤ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”

32 ይህን ነገር በግልጥ ነገራቸው፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ገለል አድርጎት ይገሥጸው ጀመር። “እንዲህ አትበል” ሲል ተቈጣው።

33 ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን ከእኔ ኋላ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብም!” ሲል ገሠጸው።


ክርስቶስን መከተል የሚጠይቀው መሥዋዕትነት
( ማቴ. 10፥38-39 ፤ 16፥24-28 ፤ ሉቃ. 9፥23-27 ፤ 14፥25-27 )

34 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤

35 ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል፤

36 ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል?

37 ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል?

38 በዚህ በከሐዲና በኃጢአተኛ ትውልድ ፊት በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ እኔም የሰው ልጅ በአባቴ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር ስመጣ በእርሱ አፍርበታለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos