ኢሳይያስ 24:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሚያስደስት የመሰንቆ፥ ሙዚቃና የአታሞ ድምፅ መሰማቱ ቀርቶአል፤ የበዓል አከባበር ሁሉ ቆሞአል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤ የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ ደስ የሚያሠኘውም በገና እረጭ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የከበሮአቸው ደስታ አልቆአል፤ መታጀራቸውም አልቃለች፤ የኃጥኣን ሀብት አልቆአል፤ የመሰንቆ ድምፅም ቀርቶአል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። |
እነሆ በፍሬያማው የእርሻ ቦታ አንድ እንኳ ደስተኛ የለም፤ በወይን ተክል ቦታዎች የእልልታና የዝማሬ ድምፅ አይሰማም፤ የወይን ጠጅ ለመጥመቅ የወይን ፍሬ የሚጨምቅ የለም፤ እግዚአብሔር የደስታ እልልታን ሁሉ እንዲቆም አድርጎአል።
እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የምልህን አድምጥ፥ አንተ ባለህበት በዚህ ዘመን የደስታና የሐሤት፥ የሠርግ ዘፈን ድምፅ እንዳይሰማ አደርጋለሁ።
የእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ በሆነችው በዔደን ውስጥ ትኖር ነበር፤ ሰርድዮን፥ ዐልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያሰጲድ፥ ሰንፔርና በሉር ተብለው በሚጠሩ የከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ የወርቅ ልብስ ትለብስ ነበር፤ ከተፈጠርክበት ጊዜ አንሥቶ ይህ ሁሉ ነበረህ።
የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፥ የዋሽንት ነፊዎችና የእምቢልታ ነፊዎች ድምፅ፥ ዳግመኛ በአንቺ አይሰማም፤ ማንኛውንም ዐይነት የእጅ ጥበብ የሚሠራ ብልኀተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ አይገኝም፤ የወፍጮም ድምፅ ከእንግዲህ በአንቺ አይሰማም።