ኢሳይያስ 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 እነሆ፥ ጌታ ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ ነዋሪዎቿንም ይበትናል። 2 በሕዝቡ ላይ የሚሆነው እንዲሁ ካህኑ ላይ ይሆናል፤ በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በአስተዳዳሪው፥ በአገልጋይቱም የሚሆነው እንዲሁ በእመቤትዋ፥ በሸማቹ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በሻጩ፥ በአበዳሪው የሚሆነው እንዲሁ በተበዳሪው፥ በዕዳ አስከፋዩም የሚሆነው እንዲሁ በዕዳ ከፋዩ ይሆናል። 3 ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ ፈጽማም ትበላሻለች፤ ጌታ ይህን ቃል ተናግሮአል። 4 ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ታላላቅ ሕዝቦች ዛሉ። 5 ምድርም በነዋሪዎቿ ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘለዓለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል። 6 ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች፥ ነዋሪዎቿም ስለ ጥፋታቸው ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። 7 የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ግንድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። 8 የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። 9 እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክር መጠጥ የሚጠጡት መራራ ይሆንባቸዋል። 10 ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ማንም እንዳይገባበት የሁሉም ቤት ተዘጋ። 11 ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። 12 ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በፍርስራሽ ተለውጧል። 13 የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድርና በአሕዛብም መካከል ይሆናል። 14 እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ ጌታ ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። 15 ስለዚህ ጌታን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የጌታንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። 16 ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን፦ ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ከሀዲዎች ክህደትን ፈጽመዋል፤ ከሀዲዎች አስከፊ ክህደት ፈጽመዋል አልሁ። 17 በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። 18 የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና፥ ከሽብር ድምጽ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 19 ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። 20 ምድር እንደ ሰካራም ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ከብዷታል፥ ትወድቃለች፥ ደግማም አትነሣም። 21 በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ ጌታ በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። 22 በጉድጓድ እንደሚከማቹ እስረኞች በአንድነት ይከማቻሉ፤ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይቀጣሉ። 23 የሠራዊት ጌታም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚነግሥ በሽማግሌዎቹ ፊት ክብር ይሆናል፤ ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል። |