መዝሙር 137 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበምርኮ የነበሩ እስራኤላውያን ለቅሶ 1 በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ተቀምጠን፥ ጽዮንን ባስታወስናት ጊዜ አለቀስን። 2 እዚያ በገናዎቻችንን በአኻያ ዛፎች ላይ ሰቀልን። 3 የማረኩንና ሥቃይ የሚያሳዩን ሰዎች በመዘመር እንድናስደስታቸው “ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ለእኛ ዘምሩልን” አሉን። 4 ለእግዚአብሔር መቅረብ የሚገባውን መዝሙር በባዕድ አገር እንዴት እንዘምራለን? 5 ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺን ብረሳሽ በገና የምጫወትበት ቀኝ እጄ ይክዳኝ፤ 6 አንቺን ባላስታውስሽና ታላቅ ደስታዬ አድርጌ ባልቈጥርሽ ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ። 7 እግዚአብሔር ሆይ! ኢየሩሳሌም በተያዘችበት ቀን ኤዶማውያን ያደረጉትን አስብ፤ “እስከ መሠረትዋ አፈራርሳችሁ ጣሉአት!” እያሉ መጮኻቸውንም አስታውስ። 8 ባቢሎን ሆይ! አፍራሽዋ ባቢሎን! በእኛ ላይ ያደረግሽብንን የክፋት ብድራት ሁሉ በአንቺ ላይ የሚመልስብሽ የተባረከ ነው። 9 ሕፃናት ልጆችሽን እያነሣ በአለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተባረከ ነው። |