ሰቈቃወ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምምሕረት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤ ውርደታችንንም ተመልከት! 2 ርስታችን ለባዕዳን ተሰጠ፤ ቤታችን ሁሉ የባዕዳን መኖሪያ ሆኖአል፤ 3 አባቶቻችን በጠላት እጅ ተገደሉ፤ ስለዚህ እኛ አባት የሌለን፥ እነሆ እናቶቻችንም ባል አልባ ሆነው ቀርተዋል። 4 ለምንጠጣው ውሃ ዋጋ እንከፍልበታለን፤ የማገዶ እንጨት እንኳ በዋጋ መግዛት አለብን። 5 ቀንበር እንደተጫኑ እንስሶች በመነዳት እጅግ ደክመናል፤ እንድናርፍም አይፈቀድልንም። 6 በቂ ምግብ ለማግኘት ለግብጽና ለአሦር እጃችንን ሰጠን፤ 7 አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተው አለፉ፤ እኛ ግን የእነርሱን ኃጢአት እንሸከማለን። 8 ባሪያዎች ይገዙናል፤ ከእጃቸውም ሊያድነን የሚችል የለም። 9 በበረሓው ግድያ ስላለ ምግባችንን ማግኘት የምንችለው ሕይወታችንን ለአደጋ በማጋለጥ ነው። 10 ከራብ ጽናት የተነሣ ቆዳችን እንደ ምድጃ ጠቈረ። 11 ሴቶች በጽዮን ተደፈሩ በይሁዳ ከተሞችም ደናግል ተዋረዱ። 12 መሪዎች እጆቻቸው ታስረው ተንጠለጠሉ፤ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም። 13 ወጣት ወንዶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤ ወንዶች ልጆች እንጨት በመሸከም ተንገዳገዱ። 14 ሽማግሌዎች ከከተማው ሸንጎ ራቁ፤ ወጣቶች ዘፈናቸውን አቆሙ። 15 ደስታ ከልባችን ጠፍቶአል፤ በጭፈራችን ቦታ ሐዘን ተተክቶአል። 16 ክብራችን ተገፈፈ፤ እኛም ኃጢአት ስለ ሠራን ወዮልን! 17 በዚህ ምክንያት ልባችን ታመመ፤ በእነዚህም ነገሮች ምክንያት ዐይኖቻችን ደከሙ። 18 የጽዮን ተራራ ባድማ ስለ ሆነች፥ ቀበሮዎች ይመላለሱበታል። 19 አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ! ለዘለዓለም ንጉሥ ነህ፤ ዙፋንህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። 20 ታዲያ፥ ለምን በፍጹም ዝም አልከን? ለምንስ ይህን ያኽል ጊዜ ተውከን? 21 እግዚአብሔር ሆይ! እንደገና እንቋቋም ዘንድ ወደ አንተ መልሰን! ሁኔታችንን አድሰህ እንደ ቀድሞ ዘመን አድርገው። 22 ይህን ባታደርግ ግን አንተ በፍጹም ትተኸናል፤ ከመጠን በላይም በእኛ ላይ ተቈጥተሃል ማለት ነው። |