ኤፌሶን 1:18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ለምን ዐይነት ተስፋ እንደ ተጠራችሁና ቅዱሳን የሚወርሱት ክቡር ርስት ምን ያኽል ብዙ እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልቡናችሁ ዐይን እንዲበራላችሁ እጸልያለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእርሱ የተጠራችሁበት ተስፋ ምን እንደሆን፥ ከቅዱሳንም ጋር የሚኖራችሁን የርስት ክብር ባለጠግነት ምንነት እንድታውቁ፥ የልቦናችሁ ዐይኖች እንዲበሩ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዐይነ ልቡናችሁንም ያበራላችሁ ዘንድ፥ የተጠራችሁበት ተስፋም ምን እንደ ሆነ፥ በቅዱሳንም የርስቱ ክብር ባለጸግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ፥ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ |
የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ይኖራል፤ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
ቀጥሎም “እንዳያዩ፥ እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ በዓይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ ተመልሰው እንዳይፈወሱ ይህን ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ ጆሮው የተደፈነ፥ ዐይኑም የተጨፈነ እንዲሆን አድርግ” አለኝ።
የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’
ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ በፊቱ ተንበረከከና “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው።
ይሰሙን ከነበሩትም ሴቶች አንድዋ የትያጥሮን ከተማ ተወላጅ የሆነች የቀይ ልብስ ነጋዴ፥ ልድያ የምትባል ሴት ነበረች፤ እርስዋ እግዚአብሔርን የምታመልክ ሴት ነበረች፤ ጌታም ልቡናዋን ስለ ከፈተላት ጳውሎስ የሚናገረውን ቃል ታዳምጥ ነበር፤
ዐይናቸውን እንድትከፍትላቸውና ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድታወጣቸው ከሰይጣንም ግዛት ወደ እግዚአብሔር እንድትመልሳቸው አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በእኔ በማመናቸው ምክንያት የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ፤ በተመረጡት መካከልም ርስትን ይካፈላሉ።’
ወይስ የእግዚአብሔርን የደግነቱንና የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ብዛት ትንቃለህን? እግዚአብሔር ደግነቱን ያበዛልህ አንተን ወደ ንስሓ ለመምራት እንደ ሆነ አታውቅምን?
የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው።
“ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይብራ!” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር በክርስቶስ መልክ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ክብር የማወቅ ብርሃን እንዲሰጠን ብርሃኑን በልባችን ውስጥ እንዲበራ አደረገ።
እናንተ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ግንኙነት የሌላችሁ፥ ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች የሆናችሁ፥ በዚህ ዓለምም አንዳች ተስፋ የሌላችሁ፥ ያለ እግዚአብሔር የምትኖሩ፥ ከክርስቶስም የተለያችሁ እንደ ነበራችሁ አስታውሱ።
እኔ ከቅዱሳን ሁሉ የማንስ ብሆንም እንኳ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ እንዳበሥር በእግዚአብሔር ጸጋ ይህ ዕድል ተሰጠኝ።
ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው።
ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ብቻ ነው፤ ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና በዓለም ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ የተሰበከ ነው፤ እኔ ጳውሎስም አገልጋይ የሆንኩት ለዚሁ ወንጌል ነው።
እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው።
የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው።
የምታገለውም ልባቸው ተጽናንቶና በፍቅር ተሳስረው፥ ፍጹም ማስተዋልን ሁሉ በማትረፍ የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው።
ዘወትር እየመከርናችሁና እያበረታታናችሁ መንግሥቱንና ክብሩን እንድትካፈሉ የጠራችሁ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ እንድትኖሩ ዐደራ እንዳልናችሁ ታውቃላችሁ።
እኛ ግን የብርሃን ሰዎች ስለ ሆንን ራስን በመግዛት በመጠን እንኑር፤ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቊር እንልበስ፤
ይህን በማሰብ ስለ እናንተ ሳናቋርጥ የምንጸልየው አምላካችን ለጥሪው ብቁዎች እንዲያደርጋችሁና መልካም ለማድረግ ያላችሁን ፈቃድና የእምነት ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ነው።
የእምነትን መልካም ጦርነት ተዋጋ፤ አንተ ወደ እርሱ በተጠራህ ጊዜ በብዙ ምስክሮች ፊት ትክክለኛ ምስክርነትን የሰጠኸውን ዘለዓለማዊውን ሕይወት ያዝ።
እምነታቸውን የካዱትን ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት ብርሃን በርቶላቸው ነበር፤ ሰማያዊውንም ስጦታ ቀምሰው ነበር፤ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ተካፋዮች ሆነው ነበር፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ በታላቅ ምሕረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤
ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብር የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ እርሱ ራሱ ከተቀበላችሁት መከራ ያድናችኋል፤ ይደግፋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ይመሠርታችኋልም።