Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ማርቆስ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ማስተማሩ
( ማቴ. 19፥1-12 ፤ ሉቃ. 16፥18 )

1 ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ። እጅግ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ እርሱም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ነበር።

2 ከፈሪሳውያንም ጥቂቶቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው፦ “ሰው ሚስቱን እንዲፈታ በሕግ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት።

3 ኢየሱስም “ሙሴ ስለዚህ ነገር ምን አዘዛችሁ?” አላቸው።

4 እነርሱም “ሙሴማ የፍችዋን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ፈቅዶአል፤” አሉት።

5 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሴስ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንድኖ ስለማትሰሙ ነው፤

6 ነገር ግን ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ ‘እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤

7 ስለዚህ ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፤

8 ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ፤’ ከዚያም ወዲያ ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ ይሆናሉ።

9 እንግዲህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”

10 ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እንደገና ኢየሱስን ጠየቁት፤

11 እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት የሚያገባ በሚስቱ ላይ አመንዝሮአል፤

12 እንዲሁም ባልዋን ፈታ ሌላ ወንድ የምታገባ ሴት አመንዝራ ሆናለች ማለት ነው።”


ኢየሱስ ሕፃናትን መባረኩ
( ማቴ. 19፥13-15 ፤ ሉቃ. 18፥15-17 )

13 ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሕፃናቱን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡአቸውን ሰዎች ገሠጹአቸው።

14 ኢየሱስም ይህን በማየት ተቈጥቶ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤

15 በእውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ሆኖ የማይቀበላት ከቶ አይገባባትም።”

16 ከዚህ በኋላ ሕፃናቱን ዐቀፋቸውና እጁን ጭኖ ባረካቸው።


የምድር ሀብትና የእግዚአብሔር መንግሥት
( ማቴ. 19፥16-30 ፤ ሉቃ. 18፥18-30 )

17 ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ በፊቱ ተንበረከከና “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው።

18 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤

19 ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ እነርሱም ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታል፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤’ የተባሉት ናቸው።”

20 ሰውየውም “መምህር ሆይ፥ እነዚህንማ ትእዛዞች ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለው።

21 ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ እንዲህም አለው፦ “አንድ ነገር ብቻ ቀርቶሃል፤ ሂድ፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘብህን ለድኾች ስጥ፤ የተከማቸ ሀብት በሰማይ ታገኛለህ፤ ከዚህም በኋላ ና፤ ተከተለኝ።”

22 ሰውየውም ይህን በሰማ ጊዜ ፊቱ በሐዘን ጠቈረ፤ ብዙ ንብረትም ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ።

23 ኢየሱስ ዘወር ብሎ ተመለከተና ደቀ መዛሙርቱን፦ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!” አላቸው።

24 ደቀ መዛሙርቱም በቃሉ ተደነቁ፤ ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆች ሆይ! ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!

25 ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።”

26 ደቀ መዛሙርቱም በጣም ተገረሙና፥ “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።

27 ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ፦ “እርግጥ ይህ ነገር በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ይቻላል፤ ለእግዚአብሔር ሁሉ ነገር ይቻለዋል፤” አላቸው።

28 ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤” አለው።

29 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ብሎ ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ርስትን የሚተው ሰው ይበልጥ ያገኛል፤

30 በዚህ ዘመን እንኳ ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችን፥ ርስትን በመቶ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል።

31 ይሁን እንጂ ፊተኞች የሆኑት ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፤ ኋለኞች የሆኑትም ፊተኞች ይሆናሉ።”


ኢየሱስ ስለ መሞቱና ከሞት ስለ መነሣት ለሦስተኛ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
( ማቴ. 20፥17-19 ፤ ሉቃ. 18፥31-34 )

32 ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ሳሉ፥ ኢየሱስ እፊት እፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ተገረሙ፤ በስተኋላ የሚከተሉትም ፈርተው ነበር። እንደገናም ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ፥ ስለሚደርስበት ነገር እንዲህ ሲል ገለጸላቸው፦

33 “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤

34 አሕዛብም ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ ነገር ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”


የያዕቆብና የዮሐንስ ልመና
( ማቴ. 20፥20-28 )

35 የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን፤” አሉት።

36 እርሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

37 እነርሱም “በመንግሥትህ ክብር አንዳችን በቀኝህ፥ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን፤” አሉት።

38 ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን (የመከራ) ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት መጠመቅ ትችላላችሁን?” አላቸው።

39 እነርሱም “አዎ፥ እንችላለን፤” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤

40 ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥን የምሰጥ እኔ አይደለሁም፤ ይህ የሚሰጠው እግዚአብሔር ላዘጋጀላቸው ሰዎች ብቻ ነው።”

41 የቀሩት ዐሥሩ ይህን ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ ተቈጡ።

42 ኢየሱስ ሁሉንም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ አለቆች የሕዝብ ገዢዎች ተብለው እንደሚጠሩና መሪዎቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ታውቃላችሁ፤

43 በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ መሆን አይገባም፤ ከመካከላችሁ ትልቅ ሊሆን የሚፈልግ፥ አገልጋያችሁ መሆን አለበት፤

44 እንዲሁም ከመካከላችሁ የበላይ ሊሆን የሚፈልግ የሁሉም ባሪያ ይሁን።

45 የሰው ልጅ እንኳ ለማገልገልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”


ኢየሱስ የዐይነ ስውሩን የበርጤሜዎስን ዐይን ማዳኑ
( ማቴ. 20፥29-34 ፤ ሉቃ. 18፥35-43 )

46 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኢያሪኮ ከተማ መጣ። አልፎም ከከተማው ወጥቶ በሚሄድበት ጊዜ እጅግ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር፤ በመንገድ ዳር ደግሞ የጤሜዎስ ልጅ የሆነ በርጤሜዎስ የሚባል አንድ ዕውር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

47 በዚያም የሚያልፈው የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን ባወቀ ጊዜ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ እባክህ ራራልኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።

48 ብዙዎቹ “ዝም በል!” ብለው ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረኝ!” እያለ ይበልጥ ጮኸ።

49 ኢየሱስም ቆመና “ጥሩት!” አለ፤ እነርሱም ዕውሩንም “በል በርታ! ተነሥ! ኢየሱስ ይጠራሃል!” አሉት።

50 እርሱም ሸማውን ጣለና ዘሎ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ ሄደ።

51 ኢየሱስም “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ዕውሩም ሰው፥ “መምህር ሆይ፥ እባክህ ዐይኔ እንዲያይ አድርግልኝ፤” አለው።

52 ኢየሱስም “በል ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎ ሄደ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos