ዘዳግም 6:18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክልና መልካም የሆነውን ሁሉ አድርግ፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንልሃል፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ በገባውም ተስፋ ቃል መሠረት መልካሚቱን ምድር ትወርሳለህ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም መልካም እንዲሆንልህና እግዚአብሔር ለአባቶችህ በመሐላ እንድትወርሳት፣ በእግዚአብሔር ፊት ተስፋ የሰጣቸውን መልካሚቱን ምድር ገብተህ ቀናና መልካም የሆነውን አድርግ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መልካም እንዲሆንልህ፥ ጌታም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርሷን እንድትወርስ በጌታ ፊት ትክክልና መልካሙን አድርግ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያወጣልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። |
እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
“ ‘ታዲያ ልጁ በአባቱ ኃጢአት ምክንያት ያልተቀጣው ስለምንድን ነው?’ ትሉ ይሆናል፤ ልጁ ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጎአል፤ ሕጌን አክብሮአል፤ ስለዚህ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤
ጥበብ ያላቸው እነዚህን ነገሮች ይረዳሉ፤ አስተዋዮችም ያውቋቸዋል፤ የእግዚአብሔር መንገድ ትክክል ነው፤ ጻድቃን ይሄዱበታል፤ ኃጢአተኞች ግን ይሰናከሉበታል።
መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት።
ለአንተና ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘለዓለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ ይህንንም ስታደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገርን ማድረግህ ነው።
እግዚአብሔር አምላካችሁ ለዘለዓለም እንድትኖሩባት በሚያወርሳችሁ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖሩ ዘንድ ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም እንዲሆንላቸው እኔ ዛሬ የማዛችሁን ሕጉንና ትእዛዞቹን ጠብቁ።”
ሁልጊዜ በዚህ ዐይነት ቢያስቡማ እንዴት መልካም ነበር! ሁልጊዜ ቢያከብሩኝና ትእዛዞቼንም ሁሉ ቢፈጽሙ ሁሉ ነገር ለእነርሱና ለዘሮቻቸው ለዘለዓለም በመልካም ሁኔታ በተከናወነላቸው ነበር።
“እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በገባላቸው የተሰፋ ቃል መሠረት አንተ ያልገነባሃቸው ታላላቅና የሚያማምሩ ከተሞች ያሉበትን ምድር ይሰጥሃል።