Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር ይገልጣል

1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይ ጠፈርም፥ የእጁን ሥራ ያውጃል።

2 አንዱ ቀን ለሌላው ቀን ያንኑ መልእክት ያስተላልፋል፤ አንዱም ሌሊት ለሌላው ሌሊት ዕውቀቱን ያካፍላል።

3 ንግግር ወይም ቃላት የላቸውም፤ ድምፃቸውም አይሰማም፤

4 ነገር ግን መልእክታቸው ወደ ዓለም ሁሉ ይሠራጫል፤ እስከ ምድር ዳርቻም ይደርሳል፤ እግዚአብሔር የፀሐይን መኖሪያ በሰማይ አደረገ።

5 ሙሽራ ከጫጒላ ቤት እንደሚወጣ ፀሐይ ብሩህ ሆኖ ይወጣል፤ ሯጭ በሩጫ ውድድር እንደሚደሰትም ደስ ይለዋል።

6 ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ ተነሥቶ ወደ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ይገሠግሣል፤ ከሙቀቱም ኀይል ሊደበቅ የሚችል ምንም ነገር የለም።


የእግዚአብሔር ሕግ

7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ለነፍስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ የታመነ ነው፤ ማስተዋል ለጐደላቸው ጥበብን ይሰጣል።

8 የእግዚአብሔር ሕግ ትክክል ነው፤ ለልብ ደስታን ይሰጣል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ለዐይን ብርሃንን ይሰጣል።

9 እግዚአብሔርን መፍራት ለዘለዓለም የሚኖር ንጽሕና ነው፤ የእግዚአብሔር ፍርዶች ሁሉ እያንዳንዳቸው እውነትና ጽድቅ ናቸው።

10 እነርሱ ከንጹሕ ወርቅ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ናቸው፤ ከማር ወለላ ይበልጥ ጣፋጮች ናቸው።

11 እንዲሁም አገልጋይህ በእነርሱ ይመከራል፤ እነርሱንም በመጠበቅ ታላቅ ዋጋ ያገኛል።

12 የራሱን ስሕተት የሚያይ ማንም የለም፤ አምላኬ ሆይ! ከተሰወረ በደል አንጻኝ።

13 ኃጢአት እንዳይሠለጥንብኝ ዐውቆ ከመበደል ጠብቀኝ፤ ይህም ከሆነ ታላቅ በደል ከመሥራት ንጹሕ እሆናለሁ።

14 አምባዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ! ቃላቴና ሐሳቦቼ በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ይኑራቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos