ዮሐንስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበምንዝር የተያዘችው ሴት 1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። 2 በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ተመልሶ መጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ተቀምጦ ያስተምር ነበር። 3 የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ስታመነዝር የተያዘች ሴት አመጡና በሕዝቡ መካከል አቆሙአት። 4 ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦ “መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተይዛለች፤ 5 እንዲህ ዐይነትዋ ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ሙሴ በሕጋችን አዞናል፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” 6 ይህንንም ያሉት በእርሱ ላይ የክስ ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ፈልገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በመሬት ላይ ይጽፍ ጀመር። 7 ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ ቀና አለና፥ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ በእርስዋ ላይ ይጣል!” አላቸው። 8 ከዚህም በኋላ እንደገና ጐንበስ ብሎ በመሬት ላይ ጻፈ። 9 እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጀምሮ ሁሉም አንድ በአንድ ከዚያ ሄዱ፤ ስለዚህ ኢየሱስ በመካከል ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ። 10 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ፥ “አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ ማንም የለምን?” አላት። 11 እርስዋም “ጌታ ሆይ! ማንም የለም” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ” አላት። ኢየሱስ የዓለም ብርሃን መሆኑ 12 እንደገናም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል፤ በጨለማም አይመላለስም” ሲል ተናገራቸው። 13 ፈሪሳውያን “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት። 14 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ምንም እንኳ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁ፥ ወዴትም እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። 15 እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። 16 ብፈርድም እንኳ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነና እኔ ብቻዬን ስለማልፈርድ ፍርዴ እውነት ነው፤ 17 የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። 18 ስለዚህ እኔ ስለ ራሴ እመሰክራለሁ፤ የላከኝ አብም ስለ እኔ ይመሰክራል።” 19 በዚያን ጊዜ እነርሱ “አባትህ የት አለ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው። 20 ኢየሱስ ይህን ቃል የተናገረው በቤተ መቅደስ በገንዘብ መቀበያ ሣጥን አጠገብ ሆኖ ሲያስተምር ነው። ታዲያ፥ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም። ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 21 እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም እኔን ትፈልጉኛላችሁ፤ ነገር ግን ከነኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ እንጂ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም።” 22 የአይሁድ ባለሥልጣኖችም “ ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ ማለቱ ራሱን ሊገድል ይሆን?” ተባባሉ። 23 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም፤ 24 የእኔን ማንነት ዐውቃችሁ ባታምኑ ከእነኃጢአታችሁ የምትሞቱ ስለ ሆነ ከነኀጢአታችሁ ትሞታላችሁ ያልኳችሁ ስለዚህ ነው።” 25 እነርሱም “አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ከመጀመሪያ አንሥቼ እንደ ነገርኳችሁ ነኝ፤ 26 ስለ እናንተ የምናገረውና የምፈርደው ብዙ ነገር አለኝ፤ ይሁን እንጂ የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ለዓለም የምናገረው ከእርሱ የሰማሁትን ነው።” 27 እነርሱ ግን ስለ አብ እንደ ተናገራቸው አልገባቸውም። 28 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰውን ልጅ ከፍ አድርጋችሁ በምትሰቅሉት ጊዜ እኔ እርሱ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም አብ ያስተማረኝን እንደምናገር እንጂ በራሴ ሥልጣን ብቻ ምንም እንደማላደርግ ያን ጊዜ ታስተውላላችሁ። 29 የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ዘወትር የማደርገው እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ስለ ሆነ ብቻዬን አልተወኝም።” 30 ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ። ከኃጢአት ባርነት ነጻ ስለ መውጣት 31 ኢየሱስ በእርሱ ላመኑት አይሁድ እንዲህ አለ፤ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ትሆናላችሁ፤ 32 እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።” 33 እነርሱ ግን “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ከቶ ለማንም ባሪያ ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፥ አንተ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ የምትለን እንዴት ነው?” አሉት። 34 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው፤ 35 ባሪያ ሁልጊዜ በቤት ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ሁልጊዜ በቤት ውስጥ ይኖራል። 36 ስለዚህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ በእርግጥ ነጻ ትሆናላችሁ። 37 የአብርሃም ዘር መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38 እኔ ከአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።” 39 እነርሱም “አባታችን አብርሃም ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ ኖሮ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር፤ 40 እኔ ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41 እንግዲህ እናንተ የምትሠሩት የአባታችሁን ሥራ ነው።” እነርሱም “እኛ በምንዝር የተወለድን ዲቃላዎች አይደለንም፤ አንድ አባት አለን፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው” አሉት። 42 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆንማ እኔን በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ የላከኝ እርሱ ነው እንጂ እኔ በራሴ ሥልጣን አልመጣሁም። 43 ስለ ምን ንግግሬ አይገባችሁም? ንግግሬን ለመስማት ስለማትችሉ ነው። 44 እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ልጆች ናችሁ፤ ፍላጎታችሁም የአባታችሁን ምኞት መፈጸም ነው፤ እርሱ ከመጀመሪያ አንሥቶ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነት በእርሱ ስለሌለ ከእውነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ እርሱ ሐሰተኛና የሐሰት ሁሉ አባት ስለ ሆነ ሐሰት በሚናገርበት ጊዜ ከገዛ ራሱ አውጥቶ ይናገራል። 45 እኔ ግን እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም፤ 46 ለመሆኑ ከእናንተ ‘ኃጢአተኛ ነህ’ ብሎ የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነትን የምናገር ከሆንኩ ታዲያ፥ ለምን አታምኑኝም? 47 ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እንግዲህ እናንተ የእግዚአብሔርን ቃል የማትሰሙት ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ ነው።” ኢየሱስ ከአብርሃም በፊት የነበረ መሆኑ 48 አይሁድ “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ጋኔንም አለብህ፤ ማለታችን ልክ አይደለምን?” አሉት። 49 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ጋኔን የለብኝም፤ ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ፤ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ። 50 ይሁን እንጂ እኔ የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የእኔን መከበር የሚፈልግና የሚፈርድ ሌላ አለ። 51 እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚጠብቅ ፈጽሞ አይሞትም።” 52 አይሁድ እንዲህ አሉት፦ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን ዐወቅን፤ አብርሃም እንኳ ሞቶአል፤ ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን ‘ቃሌን የሚጠብቅ አይሞትም’ ትላለህ፤ 53 ለመሆኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያት ሞተዋል፤ ታዲያ፥ አንተ ራስህን ማንን ታደርጋለህ?” 54 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ዋጋ አይኖረውም እኔን የሚያከብረኝ አባቴ ነው፤ እርሱም ‘እናንተ አምላካችን’ የምትሉት ነው። 55 ሆኖም እናንተ እርሱን አላወቃችሁትም፤ እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ እኔ አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንኩ ነበር፤ እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56 የአባታችሁ የአብርሃም ምኞት የእኔን ቀን አይቶ ለመደሰት ነበር፤ አይቶም ተደሰተ።” 57 በዚህ ጊዜ አይሁድ፥ “አንተ ገና ኀምሳ ዓመት እንኳ አልሆነህም፤ ታዲያ እንዴት አብርሃምን አየሁ ትላለህ?” አሉት። 58 ኢየሱስም “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ፤ አሁንም፥ ወደፊትም አለሁ።” አላቸው። 59 ስለዚህ አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸውና ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ። |