ሮሜ 16:18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የገዛ ሆዳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉምና፤ በሚያሳምን ንግግርና በሽንገላ የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ሆድ ነው። በለሰለሰ አንደበታቸውና በሽንገላ የዋሆችን ያታልላሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንደእነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉም። በለዘቡና በሚያቈላምጡ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤ በነገር ማታለልና በማለዛዘብም የብዙዎች የዋሃንን ልብ ያስታሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። |
የእስራኤልም ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን ሰብስቦ፦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት።
እፍኝ ገብስና ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት ብላችሁ፥ ውሸት ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ፥ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት በመግደል፥ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት በማትረፍ በሕዝቤ ፊት አርክሳችሁኛል።
“በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ መካከል በሮችን የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥” ይላል የሠራዊት ጌታ። ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም።
“ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሌላውን ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”
መታዘዛችሁ በሁሉም ሰው ዘንድ ደርሶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ሊኖራችሁ ከሚገባ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትርቁ ብዬ እፈራለሁ።
የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚነግዱ እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናል፤ በተንኮል አንመላለስም ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናቀርባለን።
አሁን ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሳምናለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? እስከ አሁን ሰውን ደስ የማሰኝ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ ባርያ አልሆንም ነበር።
አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ ሰዎች መካከል የማያቋርጥ ጭቅጭቅን ነው፤ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን መምሰል ሀብት ማግኛ ዘዴ መስሎ ይታያቸዋል።
ለገንዘብ ከመስገብገባቸው የተነሣ ራሳቸው ያዘጋጁትን ታሪክ እያወሩ ይበዘብዙአችኋል። ፍርዳቸውም ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ ጥፋትም በእርግጥ ይጠብቃቸዋል!
እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ነውር ናቸው፥ ራሳቸውን እየመገቡ ያለ ኀፍረት ከእናንተ ጋር ይጋበዛሉ፥ በነፋስ የሚገፉ ውሃ የሌላቸው ደመናዎች፥ በበጋ ፍሬ የማያፈሩ፥ ሁለት ጊዜ የሞቱ፥ ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤
በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ይህ ነው፤ መልአኩንም ልኮ ራእዩን ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠ፤
በማደሪያዬ እንዲያቀርቡት ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቁርባኔን ስለምን ረገጣችሁ? ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቁርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር፥ ከእኔ ይልቅ ለልጆችህ ስለምን ክብር ሰጠህ?’