Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ነቢዩ ሚክያስ ውድቀትን መተንበዩ

1 ለኢዮሣፍጥም ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ እርሱም ከአክዓብ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ትስስርን አደረገ።

2 ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ እንዲሄድ አባበለው።

3 የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፦ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በጦርነቱም ላይ ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት።

4 ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፦ “የጌታን ቃል አስቀድመህ እንድትጠይቅ እለምንሃለሁ” አለው።

5 የእስራኤልም ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን ሰብስቦ፦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት።

6 ኢዮሣፍጥ ግን፦ “እንድንጠይቀው የጌታ ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ።

7 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ጌታን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ስለ እኔ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው።” ኢዮሣፍጥም፦ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው።

8 የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፦ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው።

9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር።

10 የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።

11 ነቢያትም ሁሉ፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድ፥ ለአንተም ይከናወንልሃል” እያሉ ተመሳሳይ የሆነን ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12 ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ ሚክያስን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ ድምፅ ሆነው ለንጉሡ መልካም ነገር ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ።”

13 ሚክያስም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ።

14 ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። እርሱም መለልሶ እንዲህ አለው፦ “ውጣ፥ ይከናወንልህ፤ በእጅህም ተላልፈው ይሰጣሉ።”

15 ንጉሡም፦ “በጌታ ስም ከእውነት በቀር ምንም ዓይነት ነገር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።

16 ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ”

17 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

18 ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

19 ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ እንዲወድቅ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ያታለለው ማን ነው?’ አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ።

20 መንፈስም መጣ፥ በጌታም ፊት ቆሞ፦ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። ጌታም፦ ‘በምን ዓይነት መንገድ?’ አለው።

21 እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ።’ ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘ታታልለዋለህ፤ ይከናወንልሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ።

22 እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ ጌታ በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አኑሮአል፤ ጌታም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።’”

23 የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና እንዲህ አለ፦ “የጌታ መንፈስ ከአንተ ጋር ለመነጋገር በምን ዓይነት መንገድ ከእኔ አለፈ?”

24 ሚክያስም፦ “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ይታይሃል” አለው።

25 የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤

26 እናንተም እንዲህ በሉ፦ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በወህኒ ቤት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት።’ ”

27 ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “በደህና የተመለስህ እንደሆነ ጌታ በእኔ አልተናረም።” ዳግመኛም እርሱ፦ “እናንተ ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙኝ!” አለ።


ንጉሥ አክዓብ መሸነፉና መሞቱ

28 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።

29 የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፦ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ጦርነቱም ገቡ።

30 የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበር፦ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ።”

31 የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፦ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፥ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ ጌታም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው።

32 የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።

33 አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም፦ “ተወግቻለሁና ሠረገላውን አዙር ከጦርነቱም ውስጥ አውጣኝ” አለው።

34 በዚያም ቀን ጦርነቱ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሠረገላው ላይ ራሱን አስደግፎ ተንጋለለ፤ ፀሐይም በጠለቀች ጊዜ ሞተ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos