ሰቈቃወ 1:8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፥ ስለዚህ ረክሳለች፥ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፥ እርሷም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤ ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤ ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤ እርሷ ራሷ ታጕረመርማለች፤ ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሩሳሌም ከባድ ኃጢአት ሠርታለች፤ መሳለቂያም ሆናለች፤ ዕርቃንዋን ስላዩአት የሚያከብሩአት ሁሉ ይንቁአታል፤ እርስዋ ራስዋ እየቃተተች ፊትዋን ታዞራለች። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ ረክሳለች፤ በተጨነቀችበት ቦታ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ውርደቷን አይተዋልና አቃለሉአት፤ እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች፤ ወደ ኋላዋም ዘወር አለች። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፥ ስለዚህ ረክሳለች፥ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፥ እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች። |
እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ተነቃቅለው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ስሜ እንዲጠራበት የቀደስኩትንም ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በየአገሩ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እስራኤልን መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጓታል።
ራሳቸው የሚሰጡትም መልስ ‘የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ምድር ያወጣ ጌታ አምላካቸውን በመተዋቸው ምክንያት ነው፤ ከዚህም በቀር ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት ትተው ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ የጥፋት መቅሠፍት ያመጣባቸውም ስለዚህ ነው’ የሚል ነው።”
በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆናሉ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤና ለክፉ ነገር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ድምፅህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ እንዲያደርጉም ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው።
“ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፤ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።
እንደታመመች የበኩርዋንም እንደምትወልድ ሴት የጭንቀት ድምፅ ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ታቃስታለች፥ እጆችዋንም በመዘርጋት፦ “በነፍሰ ገዳዮች ፊት ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ!” አለች።
ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እየጮኹ ያለቅሳሉ እንጀራም ይፈልጋሉ፥ ሰውነታቸውን ለማበርታት የከበረ ሀብታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፥ አቤቱ፥ ተጐሳቁያለሁና እይ፥ ተመልከትም።
ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች የሚያጽናናት የለም፥ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፥ ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች።
ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፥ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፥ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።
ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፥ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም።
እነርሱም በጥል ይቀርቡሻል፥ የድካምሽን ፍሬ ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፥ የዝሙትሽ ዕራቁትነት፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽ ይገለጣል።
የእስራኤል ቤት በበደላቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ አሕዛብ ያውቃሉ፤ እኔን ስለ በደሉኝ፥ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ።
ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ የምትጐናጸፈውን ነጭ ልብስ፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳልበትን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።
ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነት ቤትህ፥ የአባትህም ቤት ለዘለዓለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤’ አሁን ግን ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ ከእኔ ይራቅ።