ሰቈቃወ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምא አሌፍ א አሌፍ 1 በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች። ב ቤት ב ቤት 2 በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤ እንባዋ በጕንጮቿ ላይ ይወርዳል፤ ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣ የሚያጽናናት ማንም የለም፤ ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤ ጠላቶቿም ሆነዋል። ג ጊሜል ג ጊሜል 3 በመከራና በመረገጥ ብዛት ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤ በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤ የምታርፍበትንም ስፍራ ዐጣች፤ በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣ አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት። ד ዳሌት ד ዳሌት 4 የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤ በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤ በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷ ይቃትታሉ፤ ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች። ה ሄ ה ሄ 5 ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤ ጠላቶቿ ተመችቷቸዋል፤ ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል። ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣ ወደ ግዞት ሄደዋል። ו ዋው ו ዋው 6 የጽዮን ሴት ልጅ፣ ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቷታል፤ መሳፍንቷ፣ መሰማሪያ እንዳጣ ዋሊያ ናቸው፤ በአሳዳጆቻቸው ፊት፣ በድካም ሸሹ። ז ዛይን ז ዛይን 7 በተጨነቀችባቸውና በተንከራተተችባቸው ቀናት፣ ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣ ሀብት ሁሉ ታስባለች፤ ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣ የረዳት ማንም አልነበረም፤ ጠላቶቿ ተመለከቷት፤ በመፈራረሷም ሣቁ። ח ኼት ח ኼት 8 ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤ ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤ ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤ እርሷ ራሷ ታጕረመርማለች፤ ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች። ט ቴት ט ቴት 9 ርኩሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤ አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤ የሚያጽናናትም አልነበረም፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬን ተመልከት፤ ጠላት ድል አድርጓልና!” י ዮድ י ዮድ 10 ዮድ በሀብቷ ሁሉ ላይ፣ ጠላት እጁን ዘረጋ፤ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ የከለከልሃቸው፣ ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣ ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች። כ ካፍ כ ካፍ 11 እንጀራ በመፈለግ፣ ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤ በሕይወት ለመኖር፣ የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤ እኔ ተዋርጃለሁና።” ל ላሜድ ל ላሜድ 12 “እናንተ መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን? ተመልከቱ፤ እዩም፤ በጽኑ ቍጣው ቀን፣ እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣ በእኔ ላይ የደረሰውን፣ የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን? מ ሜም מ ሜም 13 “ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤ ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤ በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤ ወደ ኋላም ጣለኝ፤ ቀኑን ሙሉ በማድከም፣ ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ። נ ኑን נ ኑን 14 “ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤ በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤ በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤ ኀይሌንም አዳከመ፤ ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣ እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ። ס ሳሜክ ס ሳሜክ 15 “በውስጤ ያሉትን ጦረኞችህ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ተቃወመ፤ ጕልማሶቼን ለማድቀቅ፣ ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ፤ ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣ እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት። ע ዐዪን ע ዐዪን 16 “የማለቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ነው፤ ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፣ ሊያጽናናኝ የቀረበ፣ መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም፤ ጠላት በርትቷልና ልጆቼ ተጨንቀዋል።” פ ፌ פ ፌ 17 ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤ የሚያጽናናትም የለም፤ ጎረቤቶቹ ጠላቶቹ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር በያዕቆብ ላይ ትእዛዝ አውጥቷል፤ ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው፣ እንደ ርኩስ ነገር ተቈጠረች። צ ጻዲ צ ጻዲ 18 “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤ እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቴ፣ ተማርከው ሄደዋል። ק ቆፍ ק ቆፍ 19 “ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤ እነርሱ ግን ከዱኝ፤ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ፣ ምግብ ሲፈልጉ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ዐለቁ። ר ሬሽ ר ሬሽ 20 “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ተጨንቄአለሁ! በውስጤ ተሠቃይቼአለሁ፤ በልቤ ታውኬአለሁ፤ እጅግ ዐመፀኛ ሆኛለሁና፤ በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤ በቤትም ውስጥ ሞት አለ። ש ሲን እና ሺን ש ሲን እና ሺን 21 “ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤ የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤ አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤ አቤቱ የተናገርሃት ቀን ትምጣ፤ እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ። ת ታው ת ታው 22 “ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤ ከኀጢአቴ ሁሉ የተነሣ፣ በእኔ ላይ እንዳደረግህብኝ፣ በእነርሱም ላይ አድርግባቸው፤ የሥቃይ ልቅሶዬ በዝቷል፤ ልቤም ደክሟል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.