Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የበፍታው መታጠቅያ

1 ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራን መታጠቂያ ለእራስህ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቀው፤ በውኃም ውስጥ አትንከረው።”

2 እንደ ጌታም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁት።

3 የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እኔ መጣ

4 እንዲህም አለኝ፦ “የገዛኸውን በወገብህ ያለውን መታጠቂያ ወስድ፥ ተነሣም፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።”

5 ጌታም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግሁት።

6 ከብዙ ቀንም በኋላ ጌታ፦ “ተነሣ፥ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም እንድትሸሽገው ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ።

7 እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከዚያ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያውን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያው ተበላሽቶ ነበር፥ ለምንም አይረባም።

8 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤

9 “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አጠፋለሁ።

10 ቃሌን ለመስማት እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ሊያገለግሉአቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፥ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማይረባ እንደዚህ መታጠቂያ ይሆናሉ።

11 መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደሚጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም፥ ምስጋናና ክብር እንዲሆኑልኝ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን አልሰሙም።”


የወይን ጠጅ ማድጋው ምሳሌ

12 ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ይህን ቃል ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንደሚሞላ በእርግጥ እኛ አናውቅምን?” ይሉሃል።

13 አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ።

14 ሰውንም ከሰው ጋር፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ አላትማቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም።”


ምርኮ አይቀሬ መሆኑ

15 ስሙ፥ አድምጡም፤ ጌታ ተናግሮአልና አትታበዩ።

16 ሳትጨልም እግራችሁም በጨለሙት ተራሮች ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨልማ ሳይለውጠው፥ ለአምላካችሁ ለጌታ ክብርን ስጡ።

17 ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የጌታም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ እጅግ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች።

18 ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ፦ “የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ” በል።

19 የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል።

20 “ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ?

21 ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን?

22 በልብሽም፦ ‘እነዚህ ነገሮች ስለምን ደረሱብኝ?’ ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል።

23 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንተ ክፋትን የለመዳችሁ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።

24 ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ።

25 ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ፥ የለካሁልሽም ድርሻሽ ይህ ነው፥ ይላል ጌታ።

26 ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል።

27 አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የአመንዝራነትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos