ሕዝቅኤል 48:35 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዙሪያዋ ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ “ጌታ በዚያ አለ” ተብሎ ይጠራል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “የከተማዪቱም ዙሪያ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤ “የከተማዪቱ ስም፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ” ይሆናል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በአራቱም አቅጣጫ ያሉት የከተማይቱ የቅጽር ግንቦች ጠቅላላ ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ከአሁን በኋላ የከተማይቱ መጠሪያ ስም “እግዚአብሔር በዚያ አለ!” የሚል ይሆናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዙሪያዋም ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማዪቱ ስም፦ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ተብሎ ይጠራል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል። |
እርሱም፦ “አንተ የጌታ አምላክህን ቃል ብትሰማ፥ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እኔ ጌታ ነኝና” አለ።
ግራ እንደ ተጋባ ሰው፥ ለማዳንም እንደማይችል ኃያል ለምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ! በመካከላችን ነህ፥ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።”
በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የጌታ ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ በጌታ ስም አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልኸኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም።
እነሆ፦ “ጌታ በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርሷ መካከል የለምን?” የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። “በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድነው?”
የሰላም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ አጸናቸዋለሁ፥ አበዛቸዋለሁ፥ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘለዓለም አኖራለሁ።
በምዕራቡም በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱ የአሴር በር፥ አንዱ ደግሞ የንፍታሌም በር ነው።
በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ የተቀደሱ ይሆናሉ። የሚሠውትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ፥ በእነርሱም ውስጥ ይቀቅሉባቸዋል። በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ነጋዴ አይገኝም።
ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊት ጌታም ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።
ታላቅም ድምፅ ከሰማይ ከዙፋኑ ወጥቶ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ራሱ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸውም ይሆናል፤
ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።
ጌዴዎንም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ጌታ ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል።