ዘፀአት 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ውኃ ከዓለት እንደ ፈለቀላቸው 1 የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ጌታ እንዳዘዘ ሊጓዙ ከሲን ምድረ በዳ ተነሡ፥ በረፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። 2 ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፦ “የምንጠጣውን ውኃ ስጠን” አሉት። ሙሴም፦ “ለምን ትጣሉኛላችሁ? ጌታንስ ለምን ትፈታተናላችሁ?” አላቸው። 3 ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ፥ ሕዝቡም በሙሴ ላይ አጉረመረሙ “እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብጽ አወጣኸን?” አሉ። 4 ሙሴም፦ “ይህን ሕዝብ ምን ላድርገው? በድንጋይ ሊወግሩኝ ቀርበዋል” ብሎ ወደ ጌታ ጮኸ። 5 ጌታም ሙሴን፦ በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ የዓባይን ወንዝ የመታህበትን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ። 6 እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ከእርሱ ውኃ ይወጣል፥ ሕዝቡም ከእርሱ ይጠጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። 7 እርሱም የዚያን ስፍራ ስም ማሳህና መሪባ ብሎ ጠራው፥ ይህም ስለ እስራኤል ልጆች ጥልና “ጌታ በመካከላችን ነው ወይስ አይደለም?” በማለት ጌታን ስለተፈታተኑት ነው። አማሌቅ እስራኤልን እንደ ተዋጋና እንደ ተሸነፈ 8 አማሌቅም መጥቶ በረፊድም ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። 9 ሙሴም ኢያሱን፦ “ሰዎችን ምረጥልን፥ ከአማሌቅም ጋር ለመዋጋትም ውጣ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ” አለው። 10 ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴ፥ አሮንና ሑር ወደ ኮረብታው ጫፍ ወጡ። 11 እንዲህም ሆነ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ይበረታ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ይበረታ ነበር። 12 የሙሴ እጆች ግን ዝለው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሑርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ያዙ፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ቀጥ አሉ። 13 ኢያሱም ዓማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። 14 ጌታም ሙሴን፦ “ይህንን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ አኑረው፥ የአማሌቅን መታሰቢያ ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና” አለው። 15 ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም “ጌታ ሰንደቅ ዓላማዬ ነው” ብሎ ጠራው፤ 16 እርሱም፦ “እጅ በጌታ ዙፋን ላይ ስለጫነ የጌታ ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይሁን አለ።” |