Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሌዋውያን ወገኖችና አገልግሎታቸው

1 ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው።

2 የእስራኤልንም ሹማምንት ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ።

3 ሌዋውያንም ዕድሜአቸው ሠላሳ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ተቈጠሩ፤ በእያንዳንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ተቈጠሩ፤ ድምራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበር።

4 ከእነዚህም ውስጥ የጌታን ቤት ሥራ የሚሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ። ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ።

5 አራቱ ሺህም የደጁ ጠባቂዎች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሰሩት በዜማ ዕቃዎች ጌታን ያመሰግኑ ነበር።

6 ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው።

7 ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ።

8 የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ።

9 የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ።

10 የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ።

11 አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።

12 የቀነዓት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ።

13 የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ እንዲሆን ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘለዓለም በጌታ ፊት እንዲያጥኑና እንዲያገለግሉ፥ በስሙም ለዘለዓለም እንዲባርኩ ተለይተው ነበር።

14 የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ።

15 የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ።

16 የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ።

17 የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ።

18 የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ።

19 የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማሪያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ።

20 የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።

21 የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ።

22 አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው።

23 የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።

24 የጌታን ቤት አገልግሎት በሠሩ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ።

25 ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘለዓለም ይቀመጣል።

26 ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም።”

27 በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ።

28 “ሥራቸውም የጌታን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ በሚሰጡተት አገልግሎት አሮንን ልጆች መርዳት፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት መሥራት ነበረ።

29 ደግሞም የተቀደሰ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቁርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በመለክያ ሁሉ ያገልግሉ ነበር።

30 እንዲሁም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው ጌታን በማመስገንና በማክበር፥

31 በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በጌታ ፊት ዘወትር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ፥

32 ለጌታም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት በመጠበቅ ያገለግሉ ነበረ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos