1 ጴጥሮስ 1:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ በታላቅ ምሕረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ ከምሕረቱ ብዛት በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እና አባት ይመስገን፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። |
ከዚህ በኋላ ዳዊት ሕዝቡን “አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ!” አለ፤ መላው ጉባኤም የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ወደ መሬት ለጥ ብለውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ለንጉሡም ክብር ሰጡ።
ንጉሥ ሕዝቅያስና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች መጥተው፥ እጅግ የበዛውን የስጦታ ክምር ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔርንና የእርሱ ወገኖች የሆኑትን የእስራኤልን ሕዝብ አመሰገኑ፤
እግዚአብሔር በፊቱ ሲያልፍ እንዲህ ብሎ ዐወጀ፤ “እኔ እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነኝ፤ እኔ ለቊጣ የዘገየሁ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬና ታማኝነቴ የበዛ ነው፤
ሙታንህ ተነሥተው ሕያዋን ይሆናሉ፤ እናንተ በመቃብር ውስጥ የምትኖሩ፥ ተነሥታችሁ የደስታ መዝሙር ዘምሩ! አንጸባራቂው ጠል ምድርን እንደሚያድስ እግዚአብሔርም ከሞቱ ብዙ ጊዜ የሆናቸውን ተነሥተው በሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል።
እንዲህም ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን እንደምታደርግ ገና በአገሬ ሳለሁ ተናግሬ አልነበረምን? ከፊትህ ኰብልዬ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ያቀድኩትም በዚህ ምክንያት ነበር፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅር የተመላህ፥ ቊጣህን መልሰህ ምሕረት የምታደርግ አምላክ መሆንህን ዐውቅ ነበር።
እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነን ሳለ በልጁ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፤ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቅን በኋላ በልጁ ሕይወት አማካይነት ይበልጡን እንድናለን።
ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው አምላክ በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ አማካይነት ለሟች ሥጋችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል።
እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?
ክብር የሚገባው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን በይበልጥ ታውቁ ዘንድ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ።
ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ብቻ ነው፤ ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና በዓለም ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ የተሰበከ ነው፤ እኔ ጳውሎስም አገልጋይ የሆንኩት ለዚሁ ወንጌል ነው።
እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው።
በአምላካችንና በአባታችን ፊት እምነታችሁ የሚሠራውን፥ ለፍቅር የምታደርጉትንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ሳናቋርጥ እናስታውሳለን።
ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ታማኝ የሆነው እንደ ልጅ ሆኖ ነው፤ ቤቱም እኛ ነን፤ ቤቱ የምንሆነውም የምንተማመንበትን ነገርና የምንመካበትን ተስፋ አጽንተን ስንይዝ ነው።
እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በኢየሱስ አማካይነት እርሱን ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ትተማመናላችሁ።
ጌታ ክርስቶስን በልባችሁ አክብሩት፤ ለሕይወታችሁም ጌታ አድርጉት፤ በእናንተ ስላለውም ተስፋ ለሚጠይቃችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ ዝግጁዎች ሁኑ።
ይህም ውሃ አሁን እናንተን የሚያድን የጥምቀት ምሳሌ ነው፤ ይህ ጥምቀት የሰውነትን ዕድፍ ማስወገድ ሳይሆን ንጹሕ ኅሊናን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ልመና ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤