መዝሙር 104 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ። 2 ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። 3 በቅዱስ ስሙም ትከብራላችሁ። 4 እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፤ እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። 5 የሠራውን ድንቅ ዐስቡ፥ ተአምራቱን፥ የአፉንም ፍርድ። 6 ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ 7 እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። 8 ለዘለዓለም የሚኖር ቃል ኪዳኑን፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን ዐሰበ። 9 ለአብርሃም የሠራለትን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ 10 ለያዕቆብ ምስክርነትን አጸና። 11 ለእስራኤልም ለዘለዓለም የሚኖር ኪዳኑን፤ እንዲህም አለው፥ “ለአንተ የከነዓንን ምድር፥ የርስታችሁ ገመድ ትሆናችሁ ዘንድ እሰጣለሁ፤” 12 እነርሱ በቍጥር እጅግ ጥቂቶችና፥ በውስጧ ስደተኞች ሲሆኑ። 13 ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከነገሥታት ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። 14 ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልተወም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታቱን ገሠጸ። 15 የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ። 16 በምድር ላይ ራብን አመጣ፥ የእህልን ኀይል ሁሉ አጠፋ። 17 በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ተሸጠ፥ አገልጋይም ሆነ። 18 እግሮቹም በእግር ብረት ሰለሰሉ፥ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች። 19 ቃሉ ሳይደርስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። 20 ንጉሥ ላከ፥ ፈታውም፥ የሕዝብም አለቃ አድርጎ ሾመው። 21 የቤቱ ጌታም አደረገው፥ በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፥ 22 አለቆቹን ሁሉ እንደ እርሱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። 23 እስራኤልም ወደ ግብፅ ገባ፥ ያዕቆብም በካም ምድር ተቀመጠ። 24 ሕዝቡንም እጅግ አበዛቸው፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። 25 ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። 26 ባሪያውን ሙሴን፥ የመረጠውንም አሮንን ላከ። 27 የተአምራቱን ቃል በላያቸው ድንቁንም በካም ምድር አደረገ። 28 ጨለማንም ላከ ጨለመባቸውም፤ ቃሉንም መራራ አደረጉት። 29 ውኃቸውን ደም አደረገ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። 30 ምድራቸው በንጉሦቻቸው ቤቶች ጓጕንቸሮችን አወጣች። 31 እርሱ ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በምድራቸው ሁሉ መጡ። 32 ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ነደደ። 33 ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የሀገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 34 ተናገረ፥ አንበጣም፥ ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ መጣ፥ 35 የምድራቸውንም ፍሬ ሁሉ በላ የተግባራቸውን ሁሉ መጀመሪያ በላ፥ 36 የሀገራቸውንም በኵር ሁሉ ገደለ። 37 ከወርቅና ከብር ጋርም አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ ደዌ አልነበረም። 38 ፈርተዋቸው ነበርና ግብፅ በመውጣታቸው ደስ አላቸው። 39 ደመናን ጋርዶ ሰወራቸው። እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ። 40 ለመኑ፥ ድርጭትም መጣ፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። 41 ዓለቱን ሰነጠቀ ውኃንም አመነጨ፤ በበረሃ ወንዞች ውስጥ ሄዱ፤ 42 ለባሪያው ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን ዐስቦአልና። 43 ሕዝቡንም በደስታ የመረጣቸውንም በሐሤት አወጣ። 44 የአሕዛብንም ሀገሮች ሰጣቸው፥ የባዕድን ድካም ወረሱ፥ 45 ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዐቱንም ይፈልጉ ዘንድ። |