ምሳሌ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ለእስራኤል የነገሠ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ 2 ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የጥበብንም ቃል ለማወቅ፥ 3 የቃልን መልስ ለመቀበል በእውነት ጽድቅንም ለማወቅ ፍርድንም ለማቃናት፥ 4 ብልሃትን ለየውሃን ይሰጥ ዘንድ ለሕፃናትና ለወጣቶችም አእምሮንና ዕውቀትን፥ 5 ጠቢብ እነዚህን በመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይ ግን ምክርን ገንዘብ ያደርጋል። 6 ምሳሌንና የተሸሸገውን ነገር፥ የጠቢባንን ቃልና ዕንቈቅልሾችን ያውቃል። ምክር ለወጣቶች 7 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ዕውቀት ለሚያደርጋት ሁሉ መልካም ናት። እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፥ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። 8 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ 9 ለራስህ የክብር ዘውድን ለአንገትህም የወርቅ ድሪ ታገኛለህና። 10 ልጄ ሆይ፥ ዝንጉዎች ሰዎች አያስቱህ፤ እሽም አትበላቸው። 11 “ና ከእኛ ጋር ደምን በማፍሰስ አንድ ሁን፥ ጻድቅ ሰውንም በምድር እንቅበር፥ ብለው ቢማልዱህ፥ 12 በሕይወት ሳለ እንደ ሲኦል እንዋጠው፥ መታሰቢያውንም ከምድር እናጥፋ፤ 13 ብዙ ሀብቱን እንሰብስብ፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሙላ፤ 14 ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢትና አንድ አቁማዳ ይሁንልን” ቢሉ፥ 15 ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤ 16 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። 17 ወጥመድን ለወፎች በከንቱ የሚያጠምዱ አይደለምና፥ 18 መግደልን የለመዱ እነርሱ ክፋትን ለራሳቸው ይሰበስባሉ። የኀጢአተኞች ሰዎች አወዳደቃቸው ክፉ ነው። 19 ይህ መንገድ ኀጢአትን የሚፈጽሙ ሁሉ ነው። ቅሚያ ነፍሳቸውን ታጠፋለች። የጥበብ ጥሪ 20 ጥበብ በጎዳና ትመሰገናለች፤ በአደባባይም ድምፅዋን ትሰጣለች። 21 በግንብ ድምድማት ትሰብካለች፥ በኀያላን በሮች ታገለግላለች። በከተማ በሮች በድፍረት እንዲህ ትላለች፦ 22 “ይህን ያህል ዘመን የዋሃን ጽድቅን ሲከተሉ አያፍሩም። ሰነፎች፥ እስከ መቼ ድረስ ስሕተትን ትወዳላችሁ? ሰነፎች ስድብን የሚወዱ ናቸው፥ ሰነፎችም ሆነው ዕውቀትን ጠሉ። ለሚዘልፏቸው የተመቹ ሆኑ፤ 23 እነሆ፥ የቃሌን መንፈስ እነግራችኋለሁ፤ ቃሌንም አስተምራችኋለሁ። 24 በጠራሁ ጊዜ አልሰማችሁኝምና እጄን ዘረጋሁ፥ ማንም አላስተዋለም ነገርንም አበዛሁ፥ አልመለሳችሁልኝም፥ 25 “ምክሬን ሁሉ ናቃችሁ፥ ዘለፋዬንም አልተመለከታችሁም፥ 26 ስለዚህ እኔ በጥፋታችሁ እሥቃለሁ፤ ጥፋትም በመጣባችሁ ጊዜ ደስ ይለኛል። 27 ጭቅጭቅ ድንገት በመጣባችሁ ጊዜ፥ እንደዚሁም ጥፋታችሁ እንደ ዓውሎ ነፋስ በመጣባችሁ ጊዜ፥ ችግርና ምርኮ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ እኔ ከዚያ አለሁ። 28 ግን በጠራችሁኝ ጊዜ እኔ አልሰማችሁም፤ ክፉዎች ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም። 29 ዕውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራትን አልመረጡምና። 30 ምክሬን ይመለከቱ ዘንድ አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤ 31 ስለዚህ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ በራሳቸውም ኀጢአት ይጠግባሉ። 32 አላዋቂዎችን አለመመለሳቸው ትገድላቸዋለችና፥ ሰነፎችንም ምርመራቸው ትገድላቸዋለች። 33 የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፥ ከክፉም ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያርፋል።” |