ዕዝራ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በንጉሡ በአርተሰስታ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች ቤቶች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ትውልዳቸውም ይህ ነው፤ 2 ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶም፥ ከኢታምር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡስ፥ 3 ከሴኬንያ ልጆች፥ ከፋሮስ ልጆች ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር የተቈጠሩ መቶ አምሳ ወንዶች ናቸው። 4 ከፋሐት ሞዓብ ልጆች የዘርህያ ልጅ ኤሊሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች። 5 ከዘቱኤስ ልጆች የአዚኤል ልጅ ሴኬንያ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች። 6 ከዓዴን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋራ አምሳ ወንዶች። 7 ከኤሌም ልጆች የጎቶልያ ልጅ የሻያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። 8 ከሰፋጥያስ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዘብድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች። 9 ከኢዮአብ ልጆች የያሔኤል ልጅ አብድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች። 10 ከበዐኛ ልጆች የዮሴፍያ ልጅ ሰሎሚት፥ ከእርሱም ጋር መቶ ስድሳ ወንዶች። 11 ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሃያ ስምንት ወንዶች። 12 ከዓዝጋድ ልጆች የአቃጦን ልጅ፤ ዮሓናን፥ ከእርሱም ጋር መቶ ዐሥር ወንዶች። 13 ከኋለኞቹ ከአዶኒቃም ልጆች ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋልጥ፥ ይኢኤል፥ ሰማአያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች። 14 ከባጎዊ ልጆች ውታይና ዘቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። 15 ወደ አኅዋም ወደሚፈስስ ወንዝ ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱንም ስቈጥራቸው በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም። 16 ወደ አለቆቹም ወደ አልዓዛር፥ ወደ አርኤል፥ ወደ ሰማአያ፥ ወደ ሀሎናም፥ ወደ ያሪብ፥ ወደ ሄልናታን፥ ወደ ናታን፥ ወደ ዘካርያስ፥ ወደ ሜሱላም፥ ደግሞም ወደ ዐዋቂዎቹ ወደ ዮያሪብና ወደ ሄልናታን ላክሁ። 17 በካሲፍያ ስፍራ ወደ ነበረው ወደ አለቃው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ ለአምላካችን ቤትም አገልጋዮችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለአዶና ለወንድሞቹ ለናታኒም የሚነግሩአቸውን በአፋቸው አደረግሁ። 18 በላያችንም መልካም በሆነው በአምላካችን እጅ ከእስራኤል ልጅ ከሌዊ ልጅ ከሞሐሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሰራብያን፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንቱን ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን። 19 ደግሞም አሴብያስን፥ ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን ኢሳይያስን፥ ሃያውን ወንድሞቹንና ልጆቻቸውን። 20 ሌዋውያንንም እንዲያገለግሉ ዳዊትና አለቆቹ ከሰጡአቸው ናታኒም ውስጥ ሁለት መቶ ሃያ ናታኒምን አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በስም በስማቸው ተሰበሰቡ። 21 በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን፥ ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾምን አወጅሁ። 22 ንጉሡንም፥ “የአምላካችን እጅ በሚሹት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፤ ኀይሉና ቍጣው ግን እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው” ብለን ተናግረን ነበርና፤ በመንገድ ካለው ጠላት ያድኑን ዘንድ ጭፍራና ፈረሰኞች ከንጉሡ እለምን ዘንድ አፍሬ ነበርና። 23 ስለዚህም ነገር ጾምን፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱምሰማን። 24 ከካህናቱም አለቆች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሰራብያንና ሐሳብያን፥ ከእነርሱም ጋር ዐሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤ 25 ንጉሡና አማካሪዎቹ፥ አለቆቹም፥ በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ ያቀረቡትን፥ ለአምላካችን ቤት የቀረበውን ብሩንና ወርቁን፥ ዕቃውንም መዝኜ ሰጠኋቸው። 26 ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶም መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶም መክሊት ወርቅ፥ 27 ሃያም ባለ ሺህ ዳሪክ የወርቅ ጽዋዎች፥ ሁለትም እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩና ከሚያንጸበርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው ሰጠሁ። 28 እኔም “እናንተ ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ዕቃዎቹም ቅዱሳን ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የቀረበ ነው፤ 29 በካህናትና በሌዋውያን አለቆች፥ በእስራኤልም አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት ጓዳዎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ” አልኋቸው። 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ይወስዱት ዘንድ ብሩንና ወርቁን፥ ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ። 31 በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም እንሄድ ዘንድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን፤ የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፤ በመንገድም ከጠላትና ከሚሸምቅ ሰው እጅ አዳነን። 32 ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን። 33 በአራተኛውም ቀን ብሩና ወርቁ፥ ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኦርያ ልጅ በሜሪሞት እጅ ተመዘኑ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ፤ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያን የኢያሱ ልጅ ኢዮዛብድና የቤንዊ ልጅ ናሕድያ ነበሩ። 34 ሁሉም በቍጥርና በሚዛን ተመዘነ፤ ሚዛኑም ሁሉ በዚያ ጊዜ ተጻፈ። 35 ከምርኮም የወጡት የምርኮኞች ልጆች ለእስራኤል አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስትም አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባትም ጠቦቶች፥ ለኀጢአት መሥዋዕት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎችን አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 36 የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዙ ማዶ ላሉት ለንጉሡ ሹሞችና ገዢዎች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አከበሩ። |