ሐዋርያት ሥራ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጳውሎስም በአደባባዩ ወደአሉት ሰዎች አተኵሮ ተመለከተና፥ “እናንተ ሰዎች ወንድሞች፥ እኔስ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ እግዚአብሔርን ሳገለግል ኑሬአለሁ” አላቸው። 2 ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። 3 ጳውሎስም መልሶ፥ “አንተ የተለሰነ ግድግዳ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዝዛለህን? እግዚአብሔር በቍጣው መቅሠፍት ይመታሃል” አለው። 4 በአጠገቡ ቆመው የነበሩትም ጳውሎስን፥ “እግዚአብሔር የሾመውን ሊቀ ካህናት እንዴት ትሳደባለህ?” አሉት። 5 ጳውሎስም፥ “ወንድሞች፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላውቅም መጽሐፍ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ይላልና” አላቸው። 6 ጳውሎስም እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን እንደ ሆኑ ዐውቆ፥ “እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊ ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣትም ይፈረድብኛል” ብሎ በአደባባይ ጮኸ። 7 እንዲህም ባለ ጊዜ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ተጣሉ፤ ሸንጎውም ተከፋፈለ። 8 ሰዱቃውያን፥ “ሙታን አይነሡም፤ መልአክም የለም፤ መንፈስም የለም” ይላሉና፤ ፈሪሳውያን ግን ይህ ሁሉ እንዳለ ያምናሉ። 9 ታላቅ ውካታም ሆነ፤ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑ ጸሐፍት ተነሥተው ይጣሉና ይከራከሩ ጀመሩ፤ “በዚህ ሰው ላይ ያገኘነው ክፉ ነገር የለም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮት እንደ ሆነ እንጃ፥ ከእግዚአብሔር ጋር አንጣላ” አሉ። 10 እጅግም በታወኩ ጊዜ ጳውሎስን እንዳይነጥቁት የሻለቃው ፈራና መጥተው ከመካከላቸው አውጥተው ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ። 11 በሁለተኛዪቱም ሌሊት ጌታችን ለጳውሎስ ተገልጦ፥ “ጽና፥ በኢየሩሳሌም ምስክር እንደ ሆንኸኝ እንዲሁ በሮም ምስክር ትሆነኛለህ” አለው። 12 በነጋም ጊዜ አይሁድ ተሰብስበው፥ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተስማምተው ተማማሉ። 13 ይህንም ለማድረግ የተማማሉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር። 14 እነርሱም ወደ ሊቃነ ካህናትና ወደ መምህራን ሄደው እንዲህ አሉአቸው፥ “ጳውሎስን እስክንገድለው ድረስ እነሆ፥ እንዳንበላና እንዳንጠጣ ፈጽመን ተማምለናል። 15 አሁንም እናንተ ከሸንጎው ጋር ወደ ሻለቃው ሂዱና የምትመረምሩትና የምትጠይቁት አስመስላችሁ ጳውሎስን እንዲያመጣው ንገሩት፤ እኛ ግን ወደ እናንተ ከመድረሱ አስቀድሞ ልንገድለው ቈርጠናል።” 16 የጳውሎስም የእኅቱ ልጅ ምክራቸውን በሰማ ጊዜ ሄዶ ወደ ወታደሮች ሰፈር ገባና ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ፥ “የሚነግረው ነገር አለና ይህን ልጅ ወደ የሻለቃው አድርስልኝ” አለው። 18 የመቶ አለቃውም ልጁን ይዞ ወደ የሻለቃው ወሰደውና፥ “የሚነግርህ ስለ አለው እስረኛው ጳውሎስ ይህን ልጅ ወደ አንተ እንዳደርሰው ለመነኝ” አለው። 19 የሻለቃውም ልጁን በእጁ ይዞ ለብቻው ገለል አድርጎ፥ “የምትነግረኝ ነገሩ ምንድነው?” አለው። 20 ልጁም እንዲህ አለው፥ “አይሁድ አጥብቀህ የምትመረምረው መስለህ ጳውሎስን ነገ ወደ ሸንጎ ታወርድላቸው ዘንድ ሊማልዱህ እንዲህ መክረዋል። 21 አንተ ግን እሽ አትበላቸው፤ ሊገድሉት ሽምቀዋልና፤ እስኪገድሉትም ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ እንዲህ የተማማሉ ሰዎች ከአርባ ይበዛሉ፤ አሁንም እስክትልክላቸው ይጠብቃሉ እንጂ እነርሱ ቈርጠዋል።” 22 ከዚህም በኋላ፤ የሻለቃው፥ “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም እንዳትገልጽ” ብሎ አሰናበተው። 23 ከመቶ አለቆችም ሁለቱን ጠርቶ፥ “ከወታደሮች ሁለት መቶ ሰውና ሰባ ፈረሰኞች፥ ሁለት መቶ ቀስተኞችም ምረጡ፤ ከሌሊቱም በሦስት ሰዓት ወደ ቂሣርያ ይሂዱ” አላቸው። 24 አህያም አምጥተው ጳውሎስን በዚያ አስቀምጠው ወደ ቂሣርያ አገረ ገዢ ወደ ፊልክስ እንዲወስዱት አዘዛቸው። 25 እንዲህ የምትል ደብዳቤም ጻፈለት። 26 “ከሉስዮስ ቀላውዴዎስ፥ ለክቡር አገረ ገዢ ፊልክስ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን። 27 ይህን ሰው አይሁድ ያዙት፤ ሊገድሉትም ፈለጉ፤ ከወታደሮችም ጋር ተከላከልሁለት፥ የሮም ሰው መሆኑንም ዐውቄ አዳንሁት። 28 በምን ምክንያትም እንደሚከሱት በደሉን አውቅ ዘንድ ወደ ሸንጎ አቅርቤ መረመርሁት። 29 ስለ ሕጋቸውም ብቻ እንደ ከሰሱት ተረዳሁ፤ ለሞትና ለመታሰር የሚያበቃ ሌላ በደል ግን የለበትም። 30 አይሁድም በዚህ ሰው ላይ በመሸመቅ የሚያደርጉትን በዐወቅሁ ጊዜ ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡና በፊትህ እንዲፋረዱት አዝዣቸዋለሁ፤ ደኅና ሁን።” 31 ጭፍሮችም እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ጳውሎስንም በሌሊት ወሰዱት፤ ወደ አንቲጳጥሪስም አደረሱት። 32 በማግሥቱም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው እነርሱ ወደ ሰፈር ተመለሱ። 33 ከዚህም በኋላ ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ወደ አገረ ገዢውም ደረሱ፤ የተላከውንም ደብዳቤ ለአገረ ገዢው ሰጡት፤ ጳውሎስንም ወደ እርሱ አቀረቡት። 34 ደብዳቤውንም ካነበበ በኋላ ከማን ግዛት እንደ ሆነ ጠየቀው። ከኪልቅያ የመጣ መሆኑንም ባወቀ ጊዜ፦ 35 “እንኪያስ ከሳሾችህ ሲመጡ እንሰማሃለን” አለው፤ በሄሮድስም ግቢ እንዲጠብቁት አዘዘ። |