Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የመንኰራኵር ራእይ

1 በሠላሳኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ነበርሁ፥ ሰማያት ተከፈቱ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ።

2 ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥

3 የጌታ ቃል፥ በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ፥ ወደ ቡዚ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። በዚያም የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ሆነች፥

4 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስ መጣ፥ በዙሪያው ብርሃን ያለው መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበር፥ በእሳቱም መካከል የሚያንጸባርቅ ነገር ነበረ።

5 ከመካከልም አራት ሕያው ፍጡራን የሚመስሉ ወጡ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር።

6 እያንዳንዳቸውም አራት ፊቶች፥ እያንዳንዳቸውም አራት ክንፎች ነበራቸው።

7 እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግሮቻቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ያንጸባርቅ ነበር።

8 ከክንፎቻቸውም ስር በአራቱም ጎናቸው የሰው እጆች ነበሩ፤ አራቱም ፊቶቻቸውና ክንፎቻቸው እንዲህ ነበሩ፦

9 ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ ይነካካ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም፥ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር።

10 የፊታቸውም ምስል የሰው ፊት፥ አራቱም በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፥ በግራ በኩል የላም ፊት ነበራቸው፥ አራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።

11 ፊታቸው እንዲህ ነበረ። ክንፎቻቸውም ወደ ላይ ተዘርግተው ነበር፥ የእያንዳንዳቸውም ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ በሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር።

12 እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፥ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር።

13 የሕያዋኑም መልክ የሚነድድ የእሳት ፍም ይመስል ነበር፥ በሕያዋኑም መካከል የሚነድድ ችቦ የሚመስል ወዲህና ወዲያ ይዘዋወር ነበር፥ እሳቱም ብርሃን ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር።

14 ሕያዋኑም እንደ መብረቅ ብልጭታ ይሄዱና ይመለሱ ነበር።

15 ሕያዋኑንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ ሕያዋን አጠገብ በምድር ላይ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ።

16 የመንኰራኵሩም መልክና አሠራር የቢረሌ መልክ ይመስል ነበር፥ የአራቱም መልክ አንድ ዓይነት ነበር፥ መልካቸውና አሠራራቸው በመንኰራኵር መካከል ያለ መንኰራኵር ይመስል ነበር።

17 ሲሄዱም በአራቱም ጎናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር።

18 ጀርባቸውም ረዥምና የሚያስፈራ ነበር፥ የአራቱም ጀርባቸው ዙሪያው በዐይኖች ተሞልቶ ነበር።

19 ሕያዋኑም ሲሄዱ መንኮራኩሮቹም በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር። እንስሶቹ ከምድር ሲነሱ መንኮራኩሮቹም ይነሱ ነበር።

20 መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱም ይሄዳሉ፥ የሕያዋኑ መንፈስ በመንኮራኩሮቹ ውስጥ ስለ ነበረ መንኮራኩሮቹም በእነርሱ አጠገብ ይነሡ ነበር።

21 የሕያዋኑ መንፈስ በመንኮራኩሮቹ ውስጥ ስለ ነበረ ሲሄዱ ይሄዳሉ፥ ሲቆሙ ይቆማሉ፥ ከምድር ሲነሡ መንኮራኩሮቹም በአጠገባቸው ይነሣሉ።

22 ከሕያዋኑ ራስ በላይ የሚያስፈራ፥ ሰማይ የሚመስል፥ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ፥ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።

23 ከሰማዩም በታች ክንፎቻቸው የአንዱ ወደ ሌላው ተዘርግተው ነበር፥ እያንዳንዱም ገላውን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፎች ነበሩት።

24 ሲሄዱም የክንፎቻቸውን ድምፅ እንደ ብዙ ውኆች ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል አምላክ ድምፅ፥ እንደ ማዕበል ድምፅ፥ እንደ የታላቅ ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25 ከራሳቸው በላይ ካለው ሰማይ በላይ ድምፅ መጣ፥ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ አደረጉ።

26 ከራሳቸው በላይ ካለው ሰማይ በላይ ዙፋን የሚመስል ነበረ፥ እርሱም የሰንፔር ድንጋይ ይመስል ነበር፥ ዙፋን በሚመስለው፥ በላዩ ላይም ሰው የሚመስል ነበረ።

27 ወገቡ ከሚመስለው ወደ ላይ የሚያንጸባርቅ ነገር የሚመስል፥ ቤቱም በእሳት የተከበበ የሚመስል አየሁ፥ ወገቡ ከሚመስለው ወደ ታች ደግሞ በዙሪያው ብርሃን ያለው እሳት የሚመስል አየሁ።

28 በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንዳለ ቀስተ ደመና የሚመስል፥ በዙሪያው የከበበው ብርሃንም እንዲሁ ይመስል ነበር። ይህም የጌታ ክብር መልክ አምሳያ ነበር። ባየሁትም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገር ድምፅም ሰማሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos