1 የጠራች ጠፈርን በህዋው ላይ አጸናት፤ የሰማይም መታየት በክብሩ ነው። 2 ብርሃኑን ያሳይ ዘንድ ፀሐይን ያወጣል፤ የሰማይም ብርሃን ሥርዐቱ ድንቅ ነው ። 3 በዋዕዩም ሀገሩን ያቃጥላል፤ ዋዕዩንስ ማን ይቋቋመዋል? 4 ዋዕዩንም እሳት እንደሚነድድባት ምድጃ ያደርጋል፤ ፀሐይ ግን ከሦስት ጊዜ በላይ የበለጠ ተራሮችን ያቃጥላቸዋል። ከእርሱ የሚወጣው እሳታዊ ዋዕይ፥ የሚልከውም ብርሃን ዐይን ያጨልማል፤ 5 የፈጠረው እግዚአብሔርም ታላቅ ነው፤ በቃሉም ፈጥኖ ይሄዳል። 6 ጨረቃም ለሁሉ የዘመን መለኪያ ናት፤ ለዓለምም ሁሉ ምልክት ናት፤ በእርስዋም ቀን ይለያል። 7 በጨረቃም የበዓላት ምልክት ይታወቃል፤ ሕፀፅ እያደረገች የምታልቅ ብርሃን እርስዋ ናት። 8 ጨረቃስ እንደ ስሟ ናት፤ ዕድገትዋም ድንቅ ነው፤ በሰማይ ሠራዊት ሥርዐትም ሕፀፅንና ምላትን ማፈራረቅዋ ድንቅ ነው፤ በሰማይ ሠራዊት መካከልም ታበራለች። 9 የሰማይም ጌጥ የከዋክብት ብርሃን ነው። በእግዚአብሔር ሰማይ ለዓለም ያበራሉ። 10 በቅዱሱም ቃል በየሥርዐታቸው ጸንተው ይኖራሉ፤ ከሥርዐታቸውም ወጥተው አያልፉም። 11 ብርሃኑ ፈጽሞ ያማረ ነውና፥ ቀስተ ደመናውን አይተህ ፈጣሪውን አመስግነው። 12 በሰማይ ይከፈላል፤ ብርሃኑም ይከበዋል፤ የልዑልም እጅ ይከፍለዋል። 13 በትእዛዙ በረድ ይዘንባል፤ መብረቅም በፈቃዱ ፈጥኖ ይወርዳል። 14 ስለዚህ ነገር መዛግብቱን ይገልጣል፤ ደመናትም እንደ ወፎች ይበርራሉ። 15 በገናናነቱም ደመናትን ያጸናቸዋል፤ የበረድ ድንጋይም ይሰባበራል። 16 በመጐብኘቱም ተራሮች ይነዋወጣሉ፤ በፈቃዱም የምሥራቅ ነፋስ ይነፍሳል። 17 የመብረቁም ድምፅ ምድርን ያስፈራታል፤ የምዕራብም ነፋስ ሰውነትን ያደርቃታል፤ በረድንም እንደሚበርሩ ወፎች ይበትነዋል፤ አወራረዱም እንደ አንበጣ አወራረድ ነው። 18 የንጣቱም ውበት ለዐይን ድንቅ ነው፤ መዝነቡም ለልብ ድንቅ ነው። 19 በረድን እንደ ጨው ያፈስሰዋልና፤ ጉምንም በምድር ላይ ይበትነዋል፤ ውርጭም ከረጋ በኋላ እንደ ሻፎ የብርሌ ስባሪ ብልጭ ይላል። 20 የቀዘቀዘው የምሥራቅ ነፋስም ይነፍሳል፤ ውርጩም በውኃ ላይ ይረጋል፤ በውኃው መከማቻ ላይም ይቆማል፤ እንደ ብረት ልብስም በውኃ ላይ ይኖራል፤ ይሸፍናታልም። 21 ተራራውን ይበላል፤ ምድረ በዳውንም ያቃጥላል፤ ሣሩንም እንደ እሳት ያቃጥለዋል። 22 የሰው ሁሉ ፈውስ ፈጥኖ የሚመጣ ካፊያ ነው፤ ዝናብም ወደ ምድር በወረደ ጊዜ ደስ ያሰኛል። 23 በእርሱም ምክር ጥልቁ ይደርቃል፤ በዚያም ደሴቶችን ተከለ። 24 በባሕርም የሚሄዱ ሰዎች መከራዋን ይናገራሉ፥ እኛም ሰምተን እናደንቃለን። 25 በዚያም ሥራው ፈጽሞ ድንቅ ነው። ከብትን መግዛት በየወገኑ ነው። 26 ለበጎ መዓዛም ከእርሱ መሥዋዕት ይሠዋለታል፤ በቃሉም ሁሉ ይደረጋል። 27 ብዙ ነገርን እንናገራለን፤ መፈጸምም አንችልም፤ ነገር ግን የነገሩ ሁሉ መጨረሻ እርሱ ብቻ ነው። 28 ከፍጥረት ሁሉ እርሱ ይበልጣልና፤ እርሱን ማመስገን ምን ያህል እንችላለን? 29 እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነው፤ እጅግም ታላቅ ነው፤ ኀይሉም ድንቅ ነው። 30 ጨርሳችሁ ማመስገንን አትጠነቅቁምና፤ የተቻላችሁን ያህል እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ እርሱ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። በፍጹም ኀይላችሁም አግንኑት፤ አትደርሱበትምና እርሱን ማመስገንን ቸል አትበሉ። 31 እርሱን አይቶ የሚነግረን ማን ነው? እንደ ገናናነቱስ መጠን ማን ያገነዋል? 32 የማይታየው ከዚህ የሚበልጠው ፍጥረቱ ብዙ ነው፤ ነገር ግን ያየነው ፍጥረቱ ጥቂት ብቻ ነው። 33 እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሯልና፤ ለጻድቃንም ጥበብን ሰጣቸው። |