Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ሲራክ 44 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቀደሙ አባቶች ውዳሴ 1 የከበሩ ሰዎችንና አባቶቻችንን በዘመናቸው እናመስግናቸው። 2 እግዚአብሔር ብዙ ክብርን ሰጥቶአቸዋልና፥ ከመጀመሪያ ጀምሮ አግንኖአቸዋልና። 3 በኀይላቸው ስማቸውን ያስጠሩ፥ በጥበባቸው የሚመክሩ፥ ትንቢትንም የሚናገሩ ሰዎች በመንግሥታቸው ገዙ። 4 የአሕዛብ ነገሥታት በሰልፋቸው፥ የሕዝቡም ጸሓፊዎች በምክራቸው፥ በልባቸውም ባለ በቃላቸው ጥበብ፤ 5 ምስጋናንና ያማረ መሰንቆን የሚፈልጉ፥ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ አድርገው የሚያመሰግኑ፥ 6 ባለጸጎች የሆኑ ገንዘባቸው የሚበቃቸው፥ በቤታቸው በደኅና የሚኖሩ ሰዎችም፤ 7 እነዚህ ሁሉ በዘመናቸው የከበሩ፥ በሕይወታቸውም የተዘጋጁ ናቸው፤ 8 ከእነርሱም ውዳሴያቸው ይነገር ዘንድ፥ የከበረ ስምን የተዉ አሉ። 9 የሚያስባቸው የሌለ፥ የጠፉም፥ እንዳልተፈጠሩና እንዳልተወለዱ የሆኑም አሉ። ልጆቻቸውም ከእነርሱ ጋራ እንደ እነርሱ ጠፉ። 10 እነዚህ ግን ጽድቃቸው ያልተዘነጋችባቸው፥ ይቅርታን የተሞሉ ናቸው፤ 11 ያማረች ርስታቸውም ከልጆቻቸው ጋራ ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች። ልጆቻቸውም በሥርዐታቸው ይኖራሉ። 12 ዘራቸው ፈጥኖ ይቆማል፥ ልጆቻቸውም በእነርሱ ፋንታ ናቸው፤ 13 ዘራቸውም ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክብራቸውም አያልቅም። 14 ሥጋቸውም በሰላም ተቀበረ፤ ስማቸውም ለዘለዓለም ጸንታ ትኖራለች። 15 አሕዛብም ጥበባቸውን ይናገራሉ፤ በአሕዛብም ሸንጎ ያመሰግኗቸዋል። ስለ ሄኖክና ኖኅ 16 ሄኖክ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ እግዚአብሔርም እርሱን ሰወረው፤ ንስሓም ይገቡ ዘንድ ለትውልድ ሁሉ አብነት ሆነ። 17 ኖኅም ፍጹምና ጻድቅ ሆኖ ተገኘ፤ በጥፋትም ዘመን እርሱ ለዓለም ምክንያት ሆነ፤ የጥፋትም ውኃ በወረደ ጊዜ እርሱ ለምድር ዘር ሆኖ ቀረ። 18 የጥፋት ውኃ ሰውን ሁሉ እንዳያጠፋው፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ለዘለዓለሙ ቃል ኪዳን አደረገ። ስለ አብርሃም 19 የአሕዛብ ሁሉ አባት አብርሃም ታላቅ ነው፤ የልዑልን ሕግ የጠበቀ፥ ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን ያደረገ፥ በክብር እርሱን የሚመስል አልተገኘም። 20 እግዚአብሔርም በሰውነቱ ቃል ኪዳንን አጸናለት። በፈተነውም ጊዜ የታመነ ሆኖ ተገኘ። 21 ስለዚህም አሕዛብ በዘሩ ይባረኩ ዘንድ፥ እንደ ባሕር አሸዋም ያበዛቸው ዘንድ፥ ዘሩም እንደ ሰማይ ከዋክብት ይበዙ ዘንድ፥ ከባሕር እስከ ባሕርም ድረስ ያወርሳቸው ዘንድ፥ ከወንዞችም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ያወርሳቸው ዘንድ ቃል ኪዳንን አጸናለት፥ ይስሐቅና ያዕቆብ 22 ለይስሐቅም ስለ አባቱ ስለ አብርሃም ደግነት፥ ለሰው ሁሉ የምትሆን በረከትንና ቃል ኪዳንን አጸናለት። 23 በያዕቆብ ራስ ላይም ዐረፈች፥ በረከቱም ተገለጠችለት፥ እርሷንም ርስት አድርጎ ሰጠው፤ ርስታቸውንም በየወገናቸው ለየላቸው፥ ለዐሥራ ሁለቱ ነገድም ርስታቸውን ከፈለላቸው። 24 ከእነርሱም የከበሩና በሰው ዘንድ ሞገስን ያገኙ፥ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድም የተወደዱ ጻድቃን ሰዎችን አስነሣ። |