ራእይ 7:17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዙፋኑ መካከል ያለው በግ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭም ይመራቸዋል፤ እግዚአብሔር እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ይጠርግላቸዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። |
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝቡ ሁሉ ግብዣን ያደርጋል፤ በዚህ ተራራ ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ፤ የወይን ጠጅንም ይጠጣሉ፤ ዘይትንም ይቀባሉ።
ሞት ሰዎችን ዋጠ፤ በረታም፤ እንደ ገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር በአፉ ተናግሮአልና።
ቅዱስ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን ይኖራል፤ ልቅሶን አልቅሺ፤ ይቅር በለኝም በዪ፤ ልቅሶሽን ባየ ጊዜ ይቅር ይልሻል፤ ሰምቶሻልና።
በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ፥ በረዥሙ ተራራ ሁሉ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይሆናሉ።
በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
የተጋዙትንም፦ ውጡ፤ በጨለማም የተቀመጡትን፦ ተገለጡ፤ ትል ዘንድ።” በመንገድም ሁሉ ላይ ይሰማራሉ፤ ማሰማሪያቸውም በጥርጊያ ጎዳና ሁሉ ላይ ይሆናል።
እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ።
እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ያልፋልና፤ ፀሐይሽ ከዚህ በኋላ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም አይቋረጥም።
እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም።
ሕዝቤ ሁለት ክፉ ነገሮችን አድርገዋልና፤ የሕይወት ውኃ ምንጭ እኔን ትተውኛል፥ የተነደሉትን ውኃውንም ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች ለራሳቸው ቈፍረዋል።
እያለቀሱ ሄዱ፤ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስሄዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።”
እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፥ እነርሱም ይኖራሉ፥ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።
በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።
ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው ነበር፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር” ብሎ መለሰላት።
ያቺ ሴትም እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?
እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል እንጂ።”
አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፤ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።
እንባዎችንም ሁሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዐት አልፎአልና፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።