ዘሌዋውያን 8:7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እጀ ጠባብም አለበሰው፤ በመታጠቂያም አስታጠቀው፤ የበፍታ ቀሚስም አለበሰው፤ ልብሰ መትከፍም ደረበለት፤ በልብሰ መትከፉም አሠራር ላይ በብልሃት በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ልብስም አለበሰው፥ በመርገፍም በተጌጠ ዝናር አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ የኤፉድ ማንጠልጠያ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ ኤፉዱን አሰረው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሮንን ቀሚስ አልብሶ፥ ካባ ደርቦ፥ መታጠቂያ አስታጠቀው፤ በዚያም ላይ ኤፉድ አደረገለት፤ እርሱንም በልዩ ጥበብ በተጠለፈ ቀበቶ አያይዞ በወገቡ ዙሪያ አሰረለት፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቍድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። |
የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዓ፥ ልብሰ መትከፍ፥ ቀሚስም፥ ዥንጕርጕር እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያ፥ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፥ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ።
“ልብሰ መትከፉንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከተፈተለ ከቀይ ግምጃ በግብረ መርፌ የተሠራ፥ የተለየ የሽመና ሥራ ያድርጉ።
ልብሶችን ወስደህ ለወንድምህ ለአሮን የነጭ ሐር እጀ ጠባብ ቀሚስ፥ ልብሰ መትከፍና ልብሰ እንግድዓ ታለብሰዋለህ፤ ለእርሱም ልብሰ እንግድዓውን ከልብሰ መትከፉ ጋር አያይዝለት።
በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ነፍሴም በእግዚአብሔር ሐሤት ታደርጋለች። ሽልማትን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማቷም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የደስታንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና።
እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድም ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል።
ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፤ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፤ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ።”
ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬም ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ፥ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ፥ የአባትህን ቤት ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ።