ዘሌዋውያን 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ አሮንና ስለ ልጆቹ ቅብዐተ ክህነት ( ዘፀ. 29፥1-37 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ለኀጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ መሶብ ውሰድ፤ 3 ማኅበሩንም ሁሉ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው።” 4 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩንም ሁሉ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሰበሰበ። 5 ሙሴም ማኅበሩን፥ “እግዚአብሔር ታደርጉ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው። 6 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፤ በውኃም አጠባቸው። 7 እጀ ጠባብም አለበሰው፤ በመታጠቂያም አስታጠቀው፤ የበፍታ ቀሚስም አለበሰው፤ ልብሰ መትከፍም ደረበለት፤ በልብሰ መትከፉም አሠራር ላይ በብልሃት በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። 8 ልብሰ እንግድዓውንም በእርሱ ላይ አደረገ፤ በልብሰ እንግድዓውም ላይ የምልክትና የእውነት መገለጫዎችን አኖረበት። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ አክሊል አደረገለት፤ በአክሊሉም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን የወርቅ መርገፍ አደረገ። 10 ሙሴም የቅብዐቱን ዘይት ወሰደ፤ ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ 11 ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ፤ ድንኳኒቱንና ዕቃዋን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 12 ከቅብዐቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ ቀባው፤ ቀደሰውም። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፤ የበፍታ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፤ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፤ አክሊልም ደፋላቸው። 14 የኀጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኀጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15 አረዱትም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፤ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። 16 ሙሴም በሆድ ዕቃው ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጉበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ ስባቸውንም ወሰደ፤ በመሠዊያውም ላይ ጨመረው። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቍርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 18 ሙሴም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19 ሙሴም ያን በግ አረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20 አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፥ ብልቶቹንም፥ ስቡንም ጨመረ። 21 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ ጨመረ፤ ይህ በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 22 ሙሴም ለቅድስና የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ፤ 23 አረዱትም። ሙሴም ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ቀባው። 24 የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ ቀባ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25 ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጉበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26 በእግዚአብሔር ፊት ካለው የቅድስና መሶብ አንድ የቂጣ እንጎቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27 ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቍርባንን አቀረበ፤ 28 ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አኖረው። በጎ መዓዛ የቅድስና መሥዋዕት ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 29 ሙሴም ከቅድስናው አውራ በግ ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበው ዘንድ ቈራረጠ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ። 30 ሙሴም ከቅብዐቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ከአለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። 31 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው፥ “ሥጋውን በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በተቀደሰው ቦታ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይብሉት ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ በዚያ እርሱንና በቅድስናው መሶብ ያለውን እንጀራ ብሉ። 32 ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት አቃጥሉት። 33 ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34 በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ። 35 እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐት ጠብቁ፤” 36 አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። |