ዕዝራ 4:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ጌታቸው ንጉሡ ይወቅ፤ ዐመፀኛዪቱንና እጅግም የከፋችቱን ከተማ ይሠራሉ፤ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፤ መሠረቷንም ጠገኑ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከአንተ ዘንድ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ዐመፀኛና ርኩስ ከተማ እንደ ገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጥሮቿንም እንደ ገና በመሥራትና መሠረቶቿንም በመጠገን ላይ መሆናቸው በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከአንተ ዘንድ የመጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደመጡ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ዓመፀኛይቱንና ክፉይቱን ከተማ በመስራት፥ ቅጥሮቿንም በማደስ፥ መሠረትዋንም በመጠገን ላይ ናቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ከግርማዊነትዎ ዘንድ የመጡት አይሁድ እዚህ ኢየሩሳሌም የደረሱ መሆናቸው በግርማዊነትዎ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ያቺን ዐመፀኛና ክፉ ከተማ እንደገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጽሮቹን በመጠገንና የቤተ መቅደስዋንም መሠረት በመጣል ላይ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ንጉሡ ይወቅ፤ ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋችቱን ከተማ ይሠራሉ፤ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፤ መሠረትዋንም ይጠግናሉ። |
በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወጣ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት።
ደግሞም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ።
በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዐመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጎዳች፥ ከጥንቱም የገባሮች ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፤ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር።
እኔም አዝዣለሁ፤ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዐመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዐመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ።
በዚያም ጊዜ በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ አስተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው፥ “ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የምትሠሩበትንስ ሥልጣን ማን ሰጣችሁ?” አሉአቸው።
እነዚያንም ሽማግሌዎች፦ ‘ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የምትሠሩበትንስ ሥልጣን ማን ሰጣችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው።
እነርሱም፥ “በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።
“አንተና አይሁድ ዓመፃ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል።
ከፊቱም አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ የእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
“ነቢያትን የምትገድሊያቸው፥ ወደ አንቺ የተላኩትን ሐዋርያትንም የምትደበድቢያቸው ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፍዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስባቸው ምን ያህል ወደድሁ? ነገር ግን እንቢ አላችሁ።
ይህን ሰው ሲሳደብና ወንጀል ሲሠራ፥ አይሁድንም ሁሉ በየሀገሩ ሲያውክ፥ ናዝራውያን የተባሉት ወገኖች የሚያስተምሩትንም ክህደት ሲያስተምር አግኝተነዋል።