ዕዝራ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች፥ የምርኮኞቹ ልጆች ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መቅደስ እንደሚሠሩ ሰሙ። 2 ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤቶች አለቆችም ቀርበው፥ “የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለአምላካችሁ እንሠዋለንና፥ እንደ እናንተም እንፈልገዋለንና ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሉአቸው። 3 ዘሩባቤልና ኢያሱም፥ የቀሩትም የእስራኤል አባቶች ቤቶች አለቆች፥ “የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ግን የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን” አሉአቸው። 4 የሀገሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅግ ያዳክሙ ነበር፤ እንዳይሠሩም ከለከሉአቸው፤ 5 ምክራቸውንም ያፈርሱ ዘንድ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመን ሁሉ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት ድረስ መካሪዎችን ገዙባቸው። 6 በአሕሳዊሮስም መንግሥት፥ በመንግሥቱም በመጀመሪያ ዘመን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ ደብዳቤ ጻፉ። 7 በአርተሰስታ ዘመን በሴሌም፥ ሜትሪዳጡ፥ ጣብሄል፥ የቀሩት ተባባሪውቻቸውም ለፋርስ ንጉሥ ለአርተሰስታ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። 8 አዛዡ ሬሁም፥ ጸሓፊውም ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርተሰስታ አንድ የክስ ደብዳቤ ጻፉ። 9 አዛዡ ሬሁም፥ ጸሓፊውም ሲምሳይ፥ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዲናውያን፥ አፈርሳትካዋያን፥ ጠርፈላውያን፥ አፈርሳውያን፥ አርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱስናካውያን፥ ዴሐውያን፥ ኤላማውያን፥ 10 ታላቁና ኀይለኛው አስናፍር ያፈለሳቸው፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው፥ የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ። 11 ለንጉሡ ለአርተሰስታ የላኩት የደብዳቤ ቃልም ይህ ነው፥ “በወንዝ ማዶ ያሉት ሰዎች ባሪያዎችህ፤ 12 አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ጌታቸው ንጉሡ ይወቅ፤ ዐመፀኛዪቱንና እጅግም የከፋችቱን ከተማ ይሠራሉ፤ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፤ መሠረቷንም ጠገኑ። 13 አሁንም ይህች ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንደማይሰጡ፥ ንጉሡ ይወቅ፤ ይህም መንግሥትን ይጐዳል። 14 ንጉሡንም ሲያቃልሉት ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታውቀናል፤ 15 በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዐመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጎዳች፥ ከጥንቱም የገባሮች ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፤ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። 16 ይህችም ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ሰላም እንደማይኖርህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።” 17 ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሓፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡትና ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን። 18 አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት መልእክተኛ ወደ እኔ ደረሰ 19 እኔም አዝዣለሁ፤ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዐመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዐመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። 20 በኢየሩሳሌምም እጅግ ኀያላን ነገሥታት ነበሩ፤ በወንዝም ማዶ ያለውን ሀገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና እጅ መንሻንም ይቀበሉ ነበር። 21 አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ ይህችም ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። 22 በዚህም ነገር እንዳትሳሳቱ፥ በነገሥታቱም ጕዳትና ጥፋት እንዳይበዛ ተጠንቀቁ።” 23 የንጉሡም የአርተሰስታ መልእክተኛ በደረሰ ጊዜ በአዛዡ በሬሁምና በጸሓፊው በሲምሳይ፥ በተባባሪዎቻቸውም ፊት መልእክቱን ባነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ በፈረስ ሄዱ፤ በኀይልም አስተዉአቸው። 24 በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ተቋረጠ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ። |