ዕዝራ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ 1 የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ መቅደስ እየገነቡ እንደሆነ ሰሙ። 2 ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች አለቆች ቀርበው፦ “እንደ እናንተ አምላካችሁን እንፈልገዋለን፥ የአሦር ንጉሥ ኤሳርሐዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለእርሱ እንሠዋ ነበርና፥ ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሉአቸው። 3 ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የቀሩትም የእስራኤል አባቶች አለቆች፦ “የአምላካችንን ቤት ማነፅ ለእኛና ለእናንተ አይደለም፥ እኛ ለብቻችን ሆነን ንጉሥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ እንዳዘዘን ለጌታ ለእስራኤል አምላክ ቤት እንገነባለን” አሉአቸው። 4 የምድሪቱም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይገነቡም ያስፈራሯቸው ነበር፤ 5 ከቂሮስ የፋርሱ ንጉሥ ዘመን ሁሉ ጀምሮ እስከ ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ መንግሥት ድረስ ሥራቸውን እንዲያፈርሱ ባለሥልጣኖችን ቀጠሩባቸው። የኢየሩሳሌም ዳግም መገንባት የገጠመው ተቃውሞ 6 በአሐሽኤሩስ መንግሥት፥ በመንግሥቱም መጀመሪያ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ ክስ ጻፉ። 7 በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትረዳት፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ አርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። 8 አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ ኢየሩሳሌምን የሚመለከት አንድ ደብዳቤ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ ብለው ጻፉ፤ 9 አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዳኞቹ፥ ባለሥልጣኖቹ፥ አስተዳዳሪዎቹ፥ ጸሐፍያን፥ የኤርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱሳንካውያን፥ ዴሐውያን፥ ዔላማውያን፥ 10 ታላቁና የተከበረው አስናፋር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ። 11 አሁንም የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው፦ “ለንጉሡ ለአርጤክስስ፥ አገልጋዮችህ በወንዙ ማዶ ያለ አገር የሚኖሩ ሰዎች፤ አሁንም 12 ከአንተ ዘንድ የመጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደመጡ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ዓመፀኛይቱንና ክፉይቱን ከተማ በመስራት፥ ቅጥሮቿንም በማደስ፥ መሠረትዋንም በመጠገን ላይ ናቸው። 13 አሁንም ይህች ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ ንጉሡንም እንደሚጎዳ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 14 ስለዚህ አሁን ሁላችን የቤተ መንግሥቱን ጨው እንበላለንና፥ የንጉሡ አለመከበር ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታወቅን፤ 15 በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርሷ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። 16 ይህችም ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ በወንዝ ማዶ ባለ አገር ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።” 17 ንጉሡ እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፦ “ለአዛዡ ለሬሑምና ለጸሐፊውም ለሺምሻይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ባለ አገር ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው ሰላም! አሁንም 18 ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ በግልፅ ተነበበ። 19 እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፥ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርሷም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። 20 በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። 21 አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። 22 ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለምን ይሄዳል?” 23 የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሑምና በጸሐፊው በሺምሻይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። 24 በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ። |