ሐዋርያት ሥራ 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ከሳሾች መምጣት 1 በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት። 2 ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ 3 “ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስትመሰገን አግኝተናታል። 4 ነገር ግን ነገር እንዳላበዛብህ በአጭሩ ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 5 ይህን ሰው ሲሳደብና ወንጀል ሲሠራ፥ አይሁድንም ሁሉ በየሀገሩ ሲያውክ፥ ናዝራውያን የተባሉት ወገኖች የሚያስተምሩትንም ክህደት ሲያስተምር አግኝተነዋል። 6 ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም ልንፈርድበት ፈልገን ነበር። 7 ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ጭንቅ ከእጃችን ነጥቆ ወደ አንተ ላከው። 8 ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዛቸው፤ የከሰስንበትንም ነገር ሁሉ መርምረህ ከእርሱ ልትረዳ ትችላለህ።” 9 አይሁድም፥ “እውነት ነው፤ እንዲሁ ነው” ብለው መለሱ። የጳውሎስ መልእክት 10 ሀገረ ገዢውም እንዲናገር ጳውሎስን ጠቀሰው፤ ጳውሎስም እንዲህ አለ፥ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ አስተዳዳሪ እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ጠባያቸውንም ታውቃለህ። አሁንም ደስ እያለኝ ክርክሬን አቀርባለሁ። 11 እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይሆን ልታውቀው ትችላለህ፤ 12 በምኵራብ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ቢሆን፥ በከተማም ቢሆን ሕዝብን ሳውክ፥ ከማንም ጋር ስከራከር አላገኙኝም። 13 በሚከስሱኝ ሁሉ በፊትህ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። 14 ነገር ግን ይህን አረጋግጥልሃለሁ፤ እኔ በሕግ ያለውን፥ በነቢያትም የተጻፈውን ሁሉ አምኜ እነርሱ ክህደት ብለው በሚጠሩት ትምህርት የአባቶችን አምላክ አመልከዋለሁ። 15 እነርሱም ለጻድቃንና ለኃጥኣን የሙታን ትንሣኤ ይሆን ዘንድ እንደሚጠብቁ ለእኔም እንዲሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ አለኝ። 16 እንዲሁ እኔም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ የማታወላውል ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እጋደላለሁ። 17 ከብዙ ዓመታትም በኋላ ለወገኖች ምጽዋትንና መሥዋዕትን ላደርግ መጣሁ። 18 በዚያም ጊዜ ከእስያ የመጡ አይሁድ ከሕዝብ ጋር በመከራከር፥ ወይም በፍጅት ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። 19 አሁንም በእኔ ላይ ነገር ከአላቸው ወደ አንተ ይምጡና ይክሰሱኝ። 20 ወይም እኔ በሸንጎ ቆሜ ሳለሁ ያገኙብኝ በደል እንደ አለ እነዚህ ራሳቸው ይመስክሩ። 21 በመካከላቸው ቆሜ ከአስተማርኋት አንዲት ትምህርት በቀር ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም። ‘ሙታን ይነሣሉ’ በማለቴም ዛሬ በአንተ ዘንድ በእኔ ይፈረድብኛል።” 22 ፊልክስ ግን አይሁድ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያንን ወገኖች ሕግና ትምህርት እንደሚቃወሙ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህም “እንኪያስ የሺ አለቃው ሉስዮስ በመጣ ጊዜ ነገራችሁን እናውቅ ዘንድ እንመረምራለን” ብሎ ቀጠራቸው። 23 የመቶ አለቃውንም ጳውሎስን እንዲጠብቀው፥ በሰፊ ቦታም እንዲያኖረው፥ እንዳያጠብበትም፥ ሊያገለግሉት በመጡ ጊዜም ከወዳጆቹ አንዱን ስንኳ እንዳይከለክልበት አዘዘ። 24 ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ ከአይሁዳዊት ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ። ልኮም ጳውሎስን አስጠራው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመንም የሚናገረውን ነገር ሰማው። 25 እርሱም ስለ ጽድቅና ስለ ንጽሕና፥ ስለሚመጣውም ኵነኔ በነገራቸው ጊዜ በዚህ የተነሣ ፊልክስ ፈራና ጳውሎስን፥ “አሁንስ ሂድ፤ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ” አለው። 26 ፊልክስም እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ የሚሰጠው መስሎት ነበር፤ ስለዚህ ዘወትር ይጠራውና ያነጋግረው ነበር። 27 ሁለት ዓመትም ካለፈ በኋላ፥ ፊልክስ ተሻረና ጶርቅዮስ ፊስጦስ የሚባል ሌላ ሀገረ ገዢ በእርሱ ቦታ መጣ፤ ፊልክስም በግልጥ ለአይሁድ ሊያዳላ ወደደ፤ ስለዚህም ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው። |