ነህምያ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በነህምያ ላይ የተደረገ ሴራ 1 እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንባላጥና ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። 2 ሰንባላጥና ጌሳም፥ “መጥተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ” ብለው ላኩብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ይመክሩ ነበር። 3 እኔም እንዲህ ስል መልእክተኞችን ላክሁባቸው፥ “እኔ ታላቅ ሥራ እሠራለሁ፤ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም። ስለምን ወደ እናንተ በመምጣቴና በመውረዴ ሥራው ይታጐላል? ሥራውን እንደ ፈጸምሁ እመጣለሁ።” 4 እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። 5 ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤ በእጁም ውስጥ እንዲህ የሚል ግልጥ ደብዳቤ ነበረ፦ 6 “አንተና አይሁድ ዓመፃ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። 7 ደግሞም፦ ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፤ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፤ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር።” 8 እኔም፥ “አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር አይደለም” ብዬ ላክሁበት። 9 እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፥ “እጃቸው ይደክማል” ብለው አስፈራሩን፤ ስለዚህም እጆችን አበረታሁ። 10 እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ዶልያ ልጅ ወደ ሴሜይ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና፥ “በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንግባ፤ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ በሌሊት ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና” አለኝ። 11 እኔም፥ “እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም” አልሁት። 12 እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ ዐወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር። 13 ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር። 14 አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦቢያንና ሰንባላጥን፥ ነቢይቱንም ኖዓድያን ያስፈራሩኝ ዘንድ የፈለጉትን፥ የቀሩትንም ነቢያት አስብ። የቅጥሩ ግንብ ሥራ መፈጸም 15 ቅጥሩም በኤሉል ወር በሃያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ። 16 እንዲህም ሆነ፤ ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ አይተውም እጅግ ተደናገጡ፤ ይህም ሥራ በአምላካችን እንደ ተፈጸመ አወቁ። 17 በዚያም ወራት ብዙ የይሁዳ አለቆች ወደ ጦብያ ደብዳቤዎችን ይልኩ ነበር፤ የጦብያም ደብዳቤዎች ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር። 18 ጦብያ የአራሄ ልጅ የሴኬንያ አማች ስለ ነበረ፥ ልጁም ዮሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ ስላገባ፥ በይሁዳ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበርና። 19 ደግሞም በፊቴ ስለ እርሱ መልካምነት ይናገሩ ነበር፤ የእርሱን ነገር ወደ እኔ ያመጡ ነበር፤ የእኔንም ቃል ወደ እርሱ ይወስዱ ነበር፤ ጦቢያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር። |