ዕዝራ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደ ገና መቀጠሉ 1 ነቢያቱ ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። 2 በዚያን ጊዜም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 3 በዚያም ጊዜ በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ አስተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው፥ “ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የምትሠሩበትንስ ሥልጣን ማን ሰጣችሁ?” አሉአቸው። 4 ደግሞም፥ “ይህችን ከተማስ የሚሠሩ ሰዎች ስም ማን ማን ነው?” ብለው ጠየቁአቸው። 5 የእግዚአብሔር ዐይን ግን በይሁዳ ምርኮኞች ላይ ነበረ፤ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በመልእክተኛ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም። 6 በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ አስተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቻቸውም፥ በወንዙ ማዶ የነበሩት አፈርስካውያንም ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ የላኩት የደብዳቤው ቃል ይህ ነበረ። 7 እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት፥ “ለንጉሡ ለዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤ 8 ወደ ይሁዳ ሀገር ወደ ታላቁም አምላክ ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በጥሩ ድንጋይ ይሠራል፤ በቅጥሩም ውስጥ ልዩ እንጨት ይደረጋል፤ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፤ በእጃቸውም ይከናወናል። 9 እነዚያንም ሽማግሌዎች፦ ‘ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የምትሠሩበትንስ ሥልጣን ማን ሰጣችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው። 10 ደግሞም እናስታውቅህ ዘንድ፥ በእነርሱም ያሉትን ሹሞች ስም እንጽፍልህ ዘንድ ስማቸውን ጠየቅን። 11 እንደዚህም ብለው መለሱልን፦ እኛ የሰማይና የምድር አምላክ ባሪያዎች ነን፥ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረውን፥ ታላቁም የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ ፈጽሞላቸው የነበረውን ቤት እንሠራለን። 12 አባቶቻችንም የሰማይን አምላክ ከአስቈጡ በኋላ በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፤ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። 13 ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ። 14 ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያፈለሰውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቁንና የብሩን ዕቃ ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ለቤተ መዛግብቱ ሹም ለሲሳብሳር ሰጠውና፦ 15 ‘ይህን ዕቃ ይዘህ ሂድ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ በቦታው አኑረው፤ የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ’ አለው። 16 በዚያ ጊዜም ይህ ሲሳብሳር መጣ፤ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ አልተጨረሰም። 17 አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዐይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደ ሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፤ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።” |