2 ቆሮንቶስ 1:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በእግዚአብሔር ቸርነትና ይቅርታ መመኪያችንና የነፃነታችን ምስክር ይህቺ ናትና፥ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ዓለም፥ ይልቁንም በእናንተ ዘንድ ተመላለስን። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋራ ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ትምክህታችን ይህ ነው፦ በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ባልሆነ፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት እንደኖርን፥ የሕሊናችን ምስክርነት ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። |
“አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በቅን ልብ እንደ ሄድሁ፥ በፊትህም ደስ የሚያሰኝህን እንዳደረግሁ አስብ።” ሕዝቅያስም እጅግ ታላቅ ልቅሶን አለቀሰ።
ጳውሎስም በአደባባዩ ወደአሉት ሰዎች አተኵሮ ተመለከተና፥ “እናንተ ሰዎች ወንድሞች፥ እኔስ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ እግዚአብሔርን ሳገለግል ኑሬአለሁ” አላቸው።
ክርስቶስ ወንጌልን ለመስበክ እንጂ ለማጥመቅ አልላከኝምና፥ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም።
ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን እኔ ባለሁበት አለሁ፤ ለእኔም የሰጠኝ ጸጋው ለከንቱ የሆነብኝ አይደለም፤ እኔም ከሁሉ ይልቅ ደከምሁ፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ያደረው የእግዚአብሔር ጸጋ አጸናኝ እንጂ እኔ አይደለሁም።
ይህም ትምህርታችን ከሰው የተገኘ ትምህርት አይደለም፤ የአነጋገር ጥበብም አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስ የገለጸው ትምህርት ነው እንጂ፤ መንፈሳዊ ጥበብም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሆነውን መርምረው ለሚያውቁ ለመንፈሳውያን ነው።
አሁንም በዓላችሁን አድርጉ፤ ነገር ግን እውነትና ንጽሕና ባለው እርሾ ነው እንጂ በአሮጌው እርሾ፥ በኀጢአትና በክፋት እርሾም አይደለም።
እንግዲህ ይህን የመከርሁ በውኑ የሠራሁት እንደ አላዋቂ ሰው ሆኜ ነውን? ወይስ በእኔ በኩል አዎን አዎን፥ አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የምመክረው ለሰው ይምሰል ነውን?
ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።
የእግዚአብሔርን ቃል በሌላ ቀላቅለው እንደሚሸቅጡ እንደ ብዙዎች አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላከ በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ እንናገራለን።
ነገር ግን በስውር የሚሠራውን አሳፋሪ ሥራ እንተወው፤ በተንኰልም አንመላለስ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅል፤ ለሰውም ሁሉ አርአያ ስለ መሆን እውነትን ገልጠን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን እናጽና።
በግድ የምላችሁ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ለዚህ ሥራ የሚተጉለት አሉና የፍቅራችሁን እውነተኛነት አሁን መርምሬ ተረዳሁ።
የሚሻለውን ሥራ እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ፥ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ ዕንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ፦
የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ።
“አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ።
ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤