መዝሙር 150:3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ ወድሱት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በመለከት ድምፅ አወድሱት፥ በበገናና በመሰንቆ አወድሱት። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በመለከት አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት፤ |
ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጸናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር።
ካህናቱ ሰበኒያ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ናትናኤል፣ ዓማሣይ፣ ዘካርያስ፣ በናያስና አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። አቢዳራ ይሒያ ደግሞ የታቦቱ በር ጠባቂዎች ነበሩ።
በዚህ ሁኔታ መላው የእስራኤል ሕዝብ በሆታ ቀንደ መለከትና እንቢልታ እየነፉ፣ ጸናጽል እየጸነጸሉ፣ መሰንቆና በገና እየደረደሩ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አመጡ።
ድምፀ መለከቱንና ጸናጽሉን ለማሰማት፣ ደግሞም መንፈሳዊ መዝሙር ሲዘመር ለሚጠቀሙባቸው ሌሎች መሣሪያዎች ኀላፊዎቹ ኤማንና ኤዶታም ነበሩ፤ የኤዶታምም ልጆች በሩን እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።
ዳዊት ከሰራዊቱ አለቆች ጋራ ሆኖ በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል ድምፅ እየታጀቡ ትንቢት የሚናገሩትን ከአሳፍ፣ ከኤማንና ከኤዶታም ቤተ ሰብ መካከል መርጦ መደበ፤ ይህን አገልግሎት የሚያከናውኑትም ሰዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦
መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣ “እርሱ ቸር ነው፣ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” እያሉ ዘመሩ። ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ።
የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤
እንዲሁም በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁና የወር መባቻ በዓል ስታከብሩ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በኅብረት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቱን ንፉ፤ እነዚህም በአምላካችሁ ፊት መታሰቢያ ይሆኑላችኋል። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”