1 ዜና መዋዕል 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ 15፥25–16፥3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 6፥12-19 1 ዳዊት በስሙ በተጠራችው ከተማ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔር ታቦት ቦታ አዘጋጅቶ ድንኳን ተከለ። 2 ከዚያም ዳዊት፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲሸከሙና ለዘላለም በፊቱ እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ማንም አይሸከም” ሲል አዘዘ። 3 ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ወዳዘጋጀለት ስፍራ እንዲያመጡ እስራኤልን ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4 የአሮንን ዘሮችና ሌዋውያኑንም በአንድነት ሰበሰበ፤ 5 ከቀዓት ዘሮች፣ አለቃውን ኡርኤልንና አንድ መቶ ሃያ የሥጋ ዘመዶቹን፤ 6 ከሜራሪ ዘሮች፣ አለቃውን ዓሣያንና ሁለት መቶ ሃያ የሥጋ ዘመዶቹን፤ 7 ከጌርሶን ዘሮች፣ አለቃውን ኢዩኤልንና አንድ መቶ ሠላሳ የሥጋ ዘመዶቹን፤ 8 ከኤሊጻፋን ዘሮች፣ አለቃውን ሸማያንና ሁለት መቶ የሥጋ ዘመዶቹን፤ 9 ከኬብሮን ዘሮች፣ አለቃውን ኤሊኤልንና ሰማንያ የሥጋ ዘመዶቹን፤ 10 ከዑዝኤል ዘሮች፣ አለቃውን አሚናዳብንና አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት የሥጋ ዘመዶቹን። 11 ከዚያም ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፣ ሌዋውያኑን ኡርኤልን፣ ዓሣያን፣ ኢዩኤልን፣ ሸማያን፣ ኤሊኤልንና አሚናዳብን ጠርቶ፣ 12 እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ እናንተ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ስለ ሆናችሁ፣ እናንተና ወንድሞቻችሁ ሌዋውያን ራሳችሁን ቀድሱ፤ ከዚያም የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ወዳዘጋጀሁለት ቦታ አምጡ። 13 የአምላካችን የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችን ላይ እንዲህ የነደደው እናንተ ሌዋውያኑ ቀድሞም ስላላመጣችሁት ነው፤ እኛም ብንሆን ምን ማድረግ እንዳለብን በታዘዘው መሠረት አልጠየቅነውም።” 14 ስለዚህ ካህናቱና ሌዋውያኑ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት ራሳቸውን ቀደሱ። 15 ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው፣ ሌዋውያኑ የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎች አድርገው ተሸከሙ። 16 ዳዊትም በዜማ መሣሪያ፣ ማለትም በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል እየታጀቡ የደስታ ዜማዎችን የሚያዜሙ መዘምራንን ከወንድሞቻቸው መካከል እንዲሾሙ ለሌዋውያኑ መሪዎች ነገራቸው። 17 ስለዚህ ሌዋውያኑ የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን ሾሙ፤ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፣ ከወንድሞቻቸው ከሜራሪ ዘሮች የቂሳን ልጅ ኤታንን ሾሙ፤ 18 ከእነርሱም ጋራ ወንድሞቻቸው በደረጃ ተሾሙ፤ እነርሱም ዘካርያስ፣ ያዝኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ ዑኒን፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ መዕሤያን፣ መቲትያ፣ ኤሊፍሌሁ፣ ሚቅኔያ፣ ደግሞም በር ጠባቂዎቹ አቢዳራ ይዒኤል ነበሩ። 19 መዘምራኑ ኤማን፣ አሳፍና ኤታን በናስ ጸናጽል ድምፁን ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ ተሾሙ፤ 20 ዘካርያስ፣ ዓዝኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ ዑኒ፣ ኤልያብ፣ መዕሤያና በናያስ ደግሞ በአላሞት ቅኝት መሰንቆ ይገርፉ ነበር። 21 እንዲሁም መቲትያ፣ ኤሊፍሌሁ፣ ሚቅኔያ፣ አቢዳራ፣ ይዒኤል፣ ዓዛዝያ፣ በሺሚኒት ቅኝት በገና ይደረድሩ ነበር። 22 የዝማሬው ኀላፊ ሌዋዊው አለቃ ክናንያ ነበረ፤ ይህን ኀላፊነት የወሰደው በዝማሬ የተካነ ስለ ነበር ነው። 23 በራክያና ሕልቃና የታቦቱ በር ጠባቂዎች ነበሩ፤ 24 ካህናቱ ሰበኒያ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ናትናኤል፣ ዓማሣይ፣ ዘካርያስ፣ በናያስና አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። አቢዳራ ይሒያ ደግሞ የታቦቱ በር ጠባቂዎች ነበሩ። 25 ስለዚህ ዳዊት የእስራኤል ሽማግሌዎችና የሻለቃው አዛዦች የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ለማምጣት ሄዱ። 26 የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያን እግዚአብሔር ረድቷቸው ስለ ነበር፣ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎች ሠዉ። 27 ታቦቱን የተሸከሙት ሌዋውያን ሁሉ፣ መዘምራኑና የመዘምራኑ አለቃ ክናንያ የለበሱትን ዐይነት ከቀጭን በፍታ የተሠራ ልብስ ዳዊትም ለብሶ ነበር፤ እንዲሁም ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ ነበር። 28 በዚህ ሁኔታ መላው የእስራኤል ሕዝብ በሆታ ቀንደ መለከትና እንቢልታ እየነፉ፣ ጸናጽል እየጸነጸሉ፣ መሰንቆና በገና እየደረደሩ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አመጡ። 29 የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡ ዳዊት ሲደሰትና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.