ዘኍል 29:6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነዚህ እንግዲህ በተደነገገው መሠረት ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ በየዕለቱና በየወሩ ከሚቀርቡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሌላ ተጨማሪ ሆነው፣ ለእግዚአብሔር ሽታቸው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቁርባን፥ ከመጠጡም ቁርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት በየወሩ መጀመሪያ ቀን ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን፥ እንዲሁም በየቀኑ ከሚቀርበው መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ታቀርባላችሁ፤ ይህም የምግብ ቊርባን ይሆናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። |
“አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድድ ይደር።
ይህም የተፈጸመው ሆነ ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋራ ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ።
መሥዋዕቱን ይዞ የሚመጣው ሰው በሂን አንድ አራተኛ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ያቀርባል።
ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ።
ስጦታውም፣ እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር ቢፈልግ በሕጉና በሥርዐቱ መሠረት መፈጸም አለበት፤ ለመጻተኛውም ሆነ ለአገሬው ተወላጅ የሚኖራችሁ ሕግ አንድ ይሁን።’ ”