Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የመለከት በዓል
29፥1-6 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥23-25

1 “ ‘በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራም አትሥሩበት፤ ይህም የመለከት ድምፅ የምታሰሙበት ቀናችሁ ነው።

2 እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።

3 ከወይፈኑ ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራውም በግ ጋራ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ፣ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት አቅርቡ፤

4 ከእያንዳንዱም ሰባት የበግ ጠቦት ጋራ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።

5 ማስተስረያ እንዲሆናችሁም አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ በተጨማሪ አቅርቡ።

6 እነዚህ እንግዲህ በተደነገገው መሠረት ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ በየዕለቱና በየወሩ ከሚቀርቡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሌላ ተጨማሪ ሆነው፣ ለእግዚአብሔር ሽታቸው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ናቸው።


የማስተስረያ ቀን
29፥7-11 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-34 ፤ 23፥26-32

7 “ ‘በዚሁ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፤ ሥራም አትሥሩ።

8 ሁሉም እንከን የሌለባቸው አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።

9 ከወይፈኑ ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራ በጉ ጋራ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ዱቄት አቅርቡ፤

10 ከሰባቱ የበግ ጠቦቶችም ከእያንዳንዳቸው ጋራ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።

11 ማስተስረያ እንዲሆንም ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው እንዲሁም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ቀርቦ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።


የዳስ በዓል
29፥12-39 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥33-43 ፤ ዘዳ 16፥13-17

12 “ ‘በሰባተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራ አትሥሩ፤ ለእግዚአብሔርም የሰባት ቀን በዓል አክብሩ።

13 ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ እንዲያሰኝ በእሳት አቅርቡ።

14 ከዐሥራ ሦስቱ ወይፈኖች ከእያንዳንዳቸው ጋራ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከሁለቱ አውራ በጎችም ከእያንዳንዳቸው ጋራ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አቅርቡ፤

15 እንዲሁም ከዐሥራ አራቱ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋራ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አቅርቡ።

16 ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

17 “ ‘በሁለተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

18 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋራ በተወሰነው ቍጥር መሠረት የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን ዐብራችሁ አቅርቡ።

19 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

20 “ ‘በሦስተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

21 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተወሰነው ቍጥር መሠረት ዐብራችሁ አቅርቡ።

22 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

23 “ ‘በአራተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዐሥር ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

24 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተደነገገው ቍጥር መሠረት አቅርቡ።

25 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

26 “ ‘በዐምስተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ዘጠኝ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

27 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተወሰነው ቍጥር መሠረት አቅርቡ።

28 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

29 “ ‘በስድስተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ስምንት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

30 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተወሰነው ቍጥር መሠረት አቅርቡ።

31 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

32 “ ‘በሰባተኛው ቀን ሁሉም እንከን የሌለባቸው ሰባት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎችና ዓመት የሆናቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ።

33 ከወይፈኖቹ፣ ከአውራ በጎቹና ከበግ ጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተወሰነው ቍጥር መሠረት አቅርቡ።

34 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

35 “ ‘በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራም አትሥሩ።

36 ሁሉም እንከን የሌለባቸው አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ቍርባን በእሳት አቅርቡ።

37 ከወይፈኑ፣ ከአውራ በጉና ከበግ ጠቦቶቹ ጋራ የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን በተወሰነው ቍጥር መሠረት አቅርቡ።

38 ደግሞም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

39 “ ‘ከስእለትና ከበጎ ፈቃድ ስጦታዎቻችሁ በተጨማሪ፣ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁን፣ የእህል ቍርባኖቻችሁን፣ የመጠጥ ቍርባኖቻችሁንና የኅብረት መሥዋዕቶቻችሁን በበዓላታችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።’ ”

40 ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤላውያን ነገራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos