ዘኍል 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በበዓለ መጥቅዕ የሚቀርብ መሥዋዕት ( ዘሌ. 23፥23-25 ) 1 “በሰባተኛውም ወር ከወሩ የመጀመሪያዋ ቀን ለእናንተ ይህች ዕለት የተቀደሰች ናት፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት፤ ምልክት ያለባት ቀን ትሁንላችሁ። 2 ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ከላሞች አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት፥ የበግ ጠቦቶች፥ 3 ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለበሬው ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 4 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። 5 ማስተስረያም የሚሆንላችሁን ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 6 በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። በኀጢአት ማስተስረያ ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት ( ዘሌ. 23፥26-32 ) 7 “የዚህም ወር ዐሥረኛዋ ቀን ለእናንተ የተቀደሰች ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቁአት፤ ከሥራ ሁሉ ምንም አታድርጉ። 8 ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ፥ ከላሞች አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑላችሁ። 9 ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለበሬው ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 10 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ፥ 11 ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። ከሚያስተሰርየው ከኀጢአት መሥዋዕት፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጥ ቍርባናቸውም ሌላ አቅርቡት። በዳስ በዓል ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት ( ዘሌ. 23፥33-44 ) 12 “በሰባተኛውም ወር ዐሥራ አምስተኛዋ ቀን ለእናንተ የተቀደሰች ትሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት፤ ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ። 13 ለእግዚአብሔርም በጎ መዓዛ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ዐሥራ ሦስት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። 14 ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለዐሥራ ሦስት በሬዎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 15 ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ዐሥረኛ እጅ፥ 16 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 17 “በሁለተኛውም ቀን ዐሥራ ሁለት በሬዎችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥ 18 ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራችው መጠን እንደ ሕጉ፥ 19 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየልን ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባናቸው ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 20 “በሦስተኛውም ቀን ዐሥራ አንድ በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 21 ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 22 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 23 “በአራተኛውም ቀን ዐሥር በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 24 ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራችው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 25 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 26 “በአምስተኛው ቀን ዘጠኝ በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸው ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 27 ለበሬዎቹና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 28 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 29 “በስድስተኛውም ቀን ስምንት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 30 ለበሬዎችና ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 31 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 32 “በሰባተኛውም ቀን ሰባት በሬዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 33 ለበሬዎቹ፥ ለአውራ በጎቹ፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው፥ 34 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 35 “ስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 36 ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በእሳት የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ በሬ፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 37 የእህል ቍርባናቸውና የመጠጥ ቍርባናቸው ለበሬው፥ ለአውራውም በግ፥ ለጠቦቶቹም እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጋቸው ይሆናሉ። 38 ለኀጢአትም መሥዋዕት ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 39 “እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም፥ ለመጠጥም ቍርባን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።” 40 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው። |