ዘኍል 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየየዕለቱ መሥዋዕት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ይህን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ስጣቸው፤ ‘ሽታው ደስ እንዲያሠኘኝ በእሳት የሚቀርብልኝን የምግብ ቍርባን የተወሰነውን ጊዜ ጠብቃችሁ አቅርቡልኝ።’ 3 ደግሞም እንዲህ በላቸው፤ ‘በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፤ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በየዕለቱ አቅርቡ። 4 አንዱን ጠቦት በማለዳ ሌላውን ደግሞ ማታ አቅርቡ፤ 5 ከዚህም ጋራ ተወቅጦ በተጠለለ በሂን አንድ አራተኛ የወይራ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ። 6 ይህም ሽታው ደስ እንዲያሰኝ በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ሲሆን፣ በሲና ተራራ የተደነገገ መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 7 ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋራ ዐብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቍርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቍርባን በተቀደሰው ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር አፍስሱት። 8 ሁለተኛውንም ጠቦት ጧት ባቀረባችሁት ዐይነት አድርጋችሁ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ ጋራ ማታ አቅርቡት፤ ይህም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። የሰንበት መሥዋዕት 9 “ ‘በሰንበት ዕለት፣ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የማይገኝባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መሥዋዕት ከመጠጥ ቍርባኑና በዘይት ከተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ጋራ አቅርቡ። 10 ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የየወሩ መሥዋዕት 11 “ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 12 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ 13 እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 14 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋራ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆን የሂን ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋራ የሂን አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋራ የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 15 ከመጠጥ ቍርባኑ ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር ይቀርባል። ፋሲካ 28፥16-25 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20 ፤ ዘሌ 23፥4-8 ፤ ዘዳ 16፥1-8 16 “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ በዓል ይከበራል። 17 በዚሁ ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ቂጣ ብሉ። 18 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት። 19 እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 20 ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ጋራ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ 21 ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋራ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ። 22 በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆናችሁ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። 23 እነዚህንም ጧት ጧት በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋራ አቅርቧቸው። 24 በዚህም ዐይነት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሆኖ በየዕለቱ ለሰባት ቀን በእሳት ለሚቀርብ መሥዋዕት የምግብ ቍርባን አዘጋጁ፤ ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋራ ሆኖ በተጨማሪ ይቀርባል። 25 በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት። የሳምንቱ በዓል 28፥26-31 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥15-22 ፤ ዘዳ 16፥9-12 26 “ ‘በሱባዔ በሚደረገው የመከር በዓል፣ አዲስ የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት በፍሬ በኵራት ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት። 27 ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። 28 ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋራ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፉ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራው በግ ጋራ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ 29 ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋራ የኢፉ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቅረብ። 30 በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ። 31 ከእህል ቍርባኑ ጋራ በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ፣ እነዚህን ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ አቅርቡ። እንስሳቱም እንከን የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጡ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.