Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለዘመን መለወጫ በዓል የሚቀርብ መሥዋዕት
( ዘሌ. 23፥23-25 )

1 “ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱም ምንም ሥራ አትሠሩበትም፤ በዚያን ቀን መለከት ይነፋል፤

2 ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ።

3 የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይኸውም ከኰርማው ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

4 ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ።

5 ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ለሕዝቡ የማስተስረይ ሥርዓት ትፈጽማላችሁ።

6 ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት በየወሩ መጀመሪያ ቀን ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን፥ እንዲሁም በየቀኑ ከሚቀርበው መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ታቀርባላችሁ፤ ይህም የምግብ ቊርባን ይሆናል።


በኃጢአት ማስተስረያ ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት
( ዘሌ. 23፥26-32 )

7 “ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በዚያን ቀን ምግብ አትመገቡም፤ ሥራም አትሠሩም፤

8 ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።

9 የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከኰርማው ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

10 ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ።

11 ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ እርሱም ለሕዝቡ የማስተስረይ ሥርዓት በተፈጸመበት ጊዜ ከሚቀርበው ተባዕት ፍየል እንዲሁም ከእህል ቊርባንና ከመጠጥ መባ፥ በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ተጨማሪ ሆኖ የሚቀርብ ነው።


በዳስ በዓል ጊዜ የሚቀርብ መሥዋዕት
( ዘሌ. 23፥33-44 )

12 “ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን በአንድነት ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ይህንንም በዓል ለእግዚአብሔር ክብር በመስጠት ሰባት ቀን አክብሩ፤ በዚህም ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ።

13 በዚህ በመጀመሪያው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት የበግ አውራዎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ አቅርቡ።

14 የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከእያንዳንዱ አውራ በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

15 ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤

16 ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት የምታቀርቡት በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ነው።

17 “በሁለተኛው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

18 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር ለየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ።

19 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

20 “በሦስተኛው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አንድ ኰርማዎች ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

21 የእህሉን ቊርባንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ።

22 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

23 “በአራተኛው ቀን ነውር የሌለባቸው ዐሥር ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

24 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኮርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ።

25 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

26 “በአምስተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ዘጠኝ ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

27 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት፥ ታቀርባላችሁ፥

28 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

29 “በስድስተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ስምንት ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ።

30 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ፤

31 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

32 “በሰባተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሰባት ኰርማዎች፥ ሁለት የአውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ።

33 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ፤

34 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

35 “በስምንተኛው ቀን በአንድነት ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በዚያም ቀን ምንም ሥራ አትሠሩም፤

36 ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ኰርማ፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።

37 የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መጠን ታቀርባላችሁ።

38 ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።

39 “በተወሰኑላችሁ በዓሎች እነዚህን ለጌታ ታቀርባላችሁ፤ ይህም ከስእለት ቊርባናችሁ፥ በፈቃዳችሁ ከምታቀርቡት መባ ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን፥ የእህል ቊርባናችሁን፥ የመጠጥ ቊርባናችሁንና የአንድነት ቊርባናችሁን ታቀርባላችሁ።”

40 በዚህ ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ ነገራቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos