ኤርምያስ 22:3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እኔ እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድና እውነት የሆነውን ነገር እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራ ጠብቁ፤ መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አታንገላቱ፤ በዚህም በተቀደሰ ስፍራ የንጹሕ ሰው ደም አታፍስሱበት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሃአደጉን፥ ባልቴቲቱንም አትበድሉ፤ አታምፁባቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፥ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። |
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን?
ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን?
እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤
የዳዊት ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ካደረጋችሁት ክፋት የተነሣ፣ ቍጣዬ እንዳይቀጣጠል፣ ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል እንዳይነድድ፣ በየማለዳው ፍትሕን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ሰው፣ ከጨቋኙ እጅ አድኑት።
ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው።
የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር።
ማንንም አይጨቍንም፤ ነገር ግን በመያዣ የወሰደውን እንኳ ለተበዳሪው ይመልሳል፤ ለተራበ የራሱን እንጀራ፣ ለተራቈተም ልብስ ይሰጣል እንጂ፣ በጕልበት አይቀማም።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤ በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣ ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።
መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤
አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።