Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ነቢዩ ኤርምያስ ንስሐ እንዲገቡ መምከሩ

1 ጌታ እንዲህ አለ፦ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥

2 እንዲህም በል፦ በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! አንተና ባርያዎችህ፥ በእነዚህም በሮች የሚገባው ሕዝብህ፥ የጌታን ቃል ስሙ።

3 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።

4 ይህንንም ነገር በጥንቃቄ ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባርያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ።

5 ነገር ግን እነዚህን ቃላት ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ባድማ እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ።

6 ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፦ አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ።

7 የጦር መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል።

8 ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፦ ጌታ በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደርገ?” ይላሉ።

9 እነርሱም፦ “የአምላካቸውን የጌታን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላገለገሉአቸውም ነዋ ብለው ይመልሳሉ።”

10 የተወለደባትንም አገር ለማየት ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና ለሚሄደው እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተው አታልቅሱ አትዘኑለትም።


ወደ ኢዮስያስ ልጆች መልእክት መምጣቱ

11 በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “ዳግመኛ ወደዚህ አይመለስም፥

12 በተማረከባት አገር በዚያ ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።”

13 “ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤

14 ‘ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ’ ለሚል፥ መስኮቶችንም ለሚያወጣለት፥ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጠው፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት!

15 በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ ይበላና ይጠጣ ፍርድንና ጽድቅን ያደርግ አልነበረምን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር።

16 የድሀውንና የችግረተኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል ጌታ።

17 ዓይንህና ልብህ ግን ለተጭበረበረ ትርፍ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።”

18 ስለዚህ ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ “ ‘ወንድሜ ሆይ! ወዮ! እህቴ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም፦ ‘ጌታ ሆይ! ወዮ! ግርማዊነቱ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም።

19 አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።”

20 “ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን ከፍ አድርጊ፤ ከዓባሪምም ሆነሽ ጩኺ።

21 በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም፦ ‘አልሰማም’ አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ድምፄን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው።

22 እረኞችሽን ሁሉ ንፋስ ያሰማራቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ኃጢአትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትዋረጃለሽም።

23 አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕመም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታቃስቻለሽ!”


በኢኮንያን ላይ የተደረገ ፍርድ

24 “እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ የማኅተም ቀለበት ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ አውልቄ እጥልህ ነበር፥ ይላል ጌታ፤

25 ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

26 አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ።

27 ለመመለስም ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።”

28 በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ማንም የማይፈልገው የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለምን ተወርውረው ተጣሉ?

29 ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! የጌታን ቃል ስሚ።

30 ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወንለት የለም፥ በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመጥ በይሁዳም የሚነግሥ ከእንግዲህ ወዲህ አይገኝምና፦ መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos