ኤርምያስ 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ስለ ታረዱት ወገኖቼ፣ ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፣ ምነው፣ ራሴ የውሃ ምንጭ በሆነ! ምነው ዐይኖቼ የእንባ መጕረፊያ በሆኑልኝ! 2 ሕዝቤን ትቼ፣ ርቄ እንድሄድ፣ በምድረ በዳ የእንግዶች ማደሪያ ማን በሰጠኝ! ሁሉም አመንዝሮች፣ የአታላዮች መንጋ ሆነዋላ! 3 “ሐሰትን ለመናገር፣ ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤ በእውነት ሳይሆን፣ በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤ ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤ እኔንም አላወቁኝም፤” ይላል እግዚአብሔር። 4 “እያንዳንዱ ወንድም አታላይ፣ ባልንጀራም ሁሉ ሐሜተኛ ስለ ሆነ፣ ወንድም ከወንድሙ ይጠንቀቅ፤ ባልንጀራም በጓደኛው አይታመን። 5 ባልንጀራ ባልንጀራውን ያታልላል፤ እውነትን የሚናገር የለም፤ ሐሰትን ይናገሩ ዘንድ ምላሳቸውን አሠልጥነዋል፤ ኀጢአትንም በማድረግ ራሳቸውን አድክመዋል። 6 መኖሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፤ ከሽንገላቸውም የተነሣ ሊያውቁኝ አልፈቀዱም፤” ይላል እግዚአብሔር። 7 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እንደ ብረት አነጥራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁም፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት፣ ከዚህ የተለየ ምን ማድረግ እችላለሁ? 8 ምላሳቸው የሚገድል ቀስት ነው፤ በሽንገላ ይናገራል፤ ሁሉም ከባልንጀራው ጋራ በሰላም ይናገራል፤ በልቡ ግን ያደባበታል። 9 ታዲያ ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “እንደዚህ ዐይነቱንስ ሕዝብ፣ አልበቀልምን?” 10 ስለ ተራሮች አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይ እላለሁ፤ በምድረ በዳ ስላሉትም መሰማሪያዎች ዐዝናለሁ። ሰው የማያልፍባቸው ባድማ ሆነዋል፤ የከብቶች ጩኸት አይሰማም፤ የሰማይ ወፎች ሸሽተዋል፤ የዱር አራዊትም ጠፍተዋል። 11 “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣ የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤ የይሁዳንም ከተሞች፣ ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” 12 ይህን መረዳት የሚችል ጥበበኛ ሰው ማን ነው? እግዚአብሔር ገልጾለት ይህንስ ማስረዳት የሚችል ማን ነው? ምድሪቱስ ሰው እንደማያልፍበት በረሓ ለምን ጠፋች? ለምን ወና ሆነች? 13 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ይህ የሆነው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተው ስላልታዘዙኝና ሥርዐቴን ስላልተከተሉ ነው። 14 በዚህ ፈንታ፣ በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን በኣሊምን ተከተሉ።” 15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ይህን ሕዝብ መራራ ምግብ አበላዋለሁ፤ የተመረዘንም ውሃ አጠጣዋለሁ። 16 እነርሱንም ሆነ አባቶቻቸውን በማያውቋቸው ሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።” 17 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እንግዲህ፤ አልቃሽ ሴቶች ጥሩ፤ ሥልጡን ሙሾ አውራጆች አስመጡ፤ 18 እነርሱ ፈጥነው ይምጡ፤ ዐይኖቻችን እንባ እስኪያጐርፉ፣ ሽፋሽፍቶቻችንም ውሃ እስኪያመነጩ፣ ስለ እኛ ሙሾ ያውርዱልን። 19 እነሆ የዋይታ ድምፅ ከጽዮን ተሰምቷል፤ እንዲህም ይላል፤ ‘ምንኛ ወደቅን! ውርደታችንስ እንዴት ታላቅ ነው! ቤቶቻችን ፈራርሰዋልና፤ አገራችንን ጥለን እንሂድ።’ ” 20 እናንተ ሴቶች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጆሮቻችሁን ከአንደበቱ ለሚወጡት ቃላት ክፈቱ፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ዋይታ፣ አንዳችሁም ሌላውን ሙሾ አስተምሩ። 21 ሞት በመስኮቶቻችን ገብቷል፤ ወደ ምሽጎቻችንም ዘልቋል፤ ሕፃናትን ከየመንገዱ፣ ወጣቶችን ከየአደባባዩ ጠራርጎ ወስዷል። 22 እንዲህ በሉ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰዎች ሬሳ፣ በሜዳ እንደ ተጣለ ጕድፍ፣ ማንም እንደማይሰበስበው፣ ከዐጫጅ ኋላ እንደ ተተወ ቃርሚያ ይወድቃል።’ ” 23 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥበበኛ በጥበቡ አይታበይ፤ ኀያልም በኀይሉ አይመካ፤ ሀብታምም በሀብቱ አይኵራራ፤ 24 የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር። 25 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሥጋቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ 26 እነርሱም ግብጽ፣ ይሁዳ፣ ኤዶም፣ አሞን፣ ሞዓብና ጠጕራቸው ዙሪያውን የሚከረከም የበረሓ ነዋሪዎች ሁሉ ናቸው፤ እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ በርግጥ የተገረዙ አይደሉምና፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው አልተገረዘም።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.