ሮሜ 1:25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህም የሆነው የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለ ለወጡ፥ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስላመለኩና ስለ አገለገሉ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም፤ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው። አሜን። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን አመለኩ አገለገሉትም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተባረከ ነው፤ አሜን። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገዋታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተዉት፤ እርሱም ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። |
ተቃጥሎ ዐመድ የሚሆነውን እንጨት እስከ ማምለክ ድረስ ሰው እንዴት ሞኝ ይሆናል? የሞኝነት አስተሳሰቡ አሳስቶታል፤ ራሱን ማዳን አይችልም፤ ወይም “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም።” ብሎ መናገር አይችልም።
ዕድል ፈንታችሁም ይህ እንደሚሆን እግዚአብሔር ተናግሮአል። እርሱን ረስታችሁ በሐሰተኞች አማልክት ስለ ታመናችሁ በእናንተ ላይ ይህን ለማድረግ ወስኖአል።
እግዚአብሔር ሆይ! የምትጠብቀኝና ብርታትን የምትሰጠኝ አንተ ነህ፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ አምባዬ ነህ፤ ሕዝቦች ከምድር ዳርቻ ሁሉ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፦ “የቀድሞ አባቶቻችን ከሐሰተኞች አማልክት በቀር ምንም አልነበራቸውም፤ ጣዖቶቻቸው ሁሉ የማይጠቅሙ ከንቱዎች ነበሩ፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕጌን ጥሰዋል፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም፤ አባቶቻቸው ይከተሉአቸው የነበሩት የሐሰት አማልክት እነርሱንም አስተዋቸዋል፤
ኧረ ለመሆኑ የጣዖት ጥቅሙ ምንድን ነው? እርሱ እኮ በሰው እጅ ተቀርጾ የተሠራ ነገር ነው፤ ከሐሰት በቀር ከእርሱ ምንም አይገኝም፤ ታዲያ እርሱን ቀርጾ የሠራው ሰው ምንም መናገር በማይችል በዚህ ጣዖት መታመኑ ምን ሊጠቅመው ነው?
ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም።
“አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ ወይም አንዱን ይጠላል፥ ሌላውንም ይወዳል፤ ወይም አንዱን ያከብራል፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ አገልጋይ መሆን አይችልም።
ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል።
የማያልፈውን እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ ኀላፊ በሆነው በሰው ምስል፥ በወፍ፥ አራት እግሮች ባሉአቸው እንስሶች፥ በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሶች መልክ ለተሠራው ምስል ክብርን ሰጡ።
እነርሱ በትውልዳቸው ከነገድ አባቶች የመጡ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የመጣው ከእነርሱ ዘር ነው፤ እርሱ ከሁሉ በላይ ነው፤ ለዘለዓለምም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን!
ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ እንዴት እንደ ተቀበላችሁን ሕያውና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖቶች ተለይታችሁ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነዚያ ሰዎች ራሳቸው ይመሰክራሉ።
እውነተኛው ትምህርት ግን የሚገኘው ስለተመሰገነው እግዚአብሔር ከሚያበሥረው ክቡር ወንጌል ነው፤ ይህም ወንጌል ለእኔ በዐደራ የተሰጠኝ ነው።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።