ሉቃስ 18:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ቀራጩ ግን በሩቅ ቆመና፥ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ለማየት እንኳ አልደፈረም፤ ነገር ግን በእጁ ደረቱን እየመታ፥ ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ!’ ይል ነበር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳን አልፈለገም፤ ነገር ግን ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ፤’ እያለ ደረቱን ይመታ ነበር። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዐይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱንም እየመታ፦ ‘አቤቱ፥ እኔን ኀጢኣተኛውን ይቅር በለኝ’ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። |
ንጉሥ ምናሴ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎትና፥ እግዚአብሔርም ለጸሎቱ የሰጠው መልስ፥ ተጸጽቶ ንስሓ ከመግባቱ በፊት ያደረገው ኃጢአት ሁሉ፥ ማለትም የፈጸመው ልዩ ልዩ ክፋት፥ እርሱ ራሱ የሠራቸው የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና አሼራ ተብላ የምትጠራው ሴት አምላክ ምስሎች፥ ያመልካቸው የነበሩ ጣዖቶች ሁሉ፥ በነቢያት የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ።
አባቱ እንዳደረገው ሁሉ ራሱን በትሕትና ዝቅ አድርጎ በማዋረድ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፤ እንዲያውም ከአባቱ ይበልጥ የከፋ ኃጢአት ሠራ።
“አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ስለ ሆነና በደላችንም ወደ ሰማይ ስለ ደረሰ ፊቴን ወደ አምላኬ ወደ አንተ ለማቅናት ዐፍራለሁ እፈራለሁም።
ከቊጥር በላይ የሆኑ ችግሮች ያስጨንቁኛል! በደሎቼ ስለ በዙ ማየት አልችልም፤ እነርሱም በቊጥር ከራስ ጠጒሮቼ ይበልጣሉ፤ ስለዚህ ልቤም እየከዳኝ ነው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስቲ ኑና እንወያይ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢቀላ እኔ አጥቤ እንደ በረዶ ይጸዳል፤ እንደ ደም የቀላ ቢሆን እንደ ባዘቶ ይነጣል።
እኔም “እነሆ አንደበቶቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል የምኖር፥ አንደበቴም የረከሰብኝ ሰው ነኝ፤ ንጉሡን የሠራዊት አምላክን በዐይኖቼ አይቼአለሁና መጥፋቴ ስለ ሆነ ወዮልኝ!” አልኩ።
እነዚህን ሁሉ ነገሮች የፈጠርኩ እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ሁሉም የእኔ ናቸው፤ እኔ የምመለከተው ልባቸው ወደ ተሰበረ፥ ትሑት መንፈስ ወዳላቸውና፥ ቃሌንም ወደሚያከብሩ ነው።
ይህንንም የማደርገው፥ ለፈጸምሽው በደል ሁሉ ይቅርታ ሳደርግልሽ ሥራሽን በማስታወስ በድንጋጤ ዐፍረሽ ጸጥ እንድትዪ ነው፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
“በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ! እነርሱ ሰው እንዲያይላቸው ብለው በየምኲራቡና በየመንገዱ ዳር ቆመው መጸለይ ይወዳሉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን በቅድሚያ አግኝተዋል።
ሂዱ፤ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት እንደ ሆነ መርምራችሁ አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው” አላቸው።
በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት።
ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ያስረዳል።
ይህ ሐዘናችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እንዴት ያለ የመከላከያ መልስ መስጠትን፥ እንዴት ያለ ቶሎ መቈጣትን፥ እንዴት ያለ ፍርሀትን፥ እንዴት ያለ ናፍቆትን፥ እንዴት ያለ ቅናትን፥ እንዴት ያለ ቅጣትንም እንዳስከተለ ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ደግሞ በሁሉም ነገር ከጉዳዩ ነጻ መሆናችሁን አስመስክራችኋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ሁሉ የባስሁ ኃጢአተኛ እኔ ነኝ።
እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ ጸጋው ወደሚገኝበት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ያለ አንዳች ፍርሀት እንቅረብ።