Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ቆሮንቶስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ፥ ይህ ሁሉ ተስፋ የተሰጠው ለእኛ ስለ ሆነ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ከማናቸውም ነገር ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችን ፍጹም እንዲሆን እናድርግ።


የጳውሎስ ደስታ

2 ከልባችሁ ተቀበሉን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አልጐዳንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም።

3 ይህንንም የምለው በእናንተ ላይ ለመፍረድ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደ ነገርኳችሁ እናንተ በልባችን ውስጥ ናችሁ፤ ስለዚህ በሕይወትም ሆነ በሞት ሁልጊዜ ከእናንተ አንለይም።

4 በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ከፍተኛ ነው፤ በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ በእናንተም እጽናናለሁ፤ በመከራችን ሁሉ በጣም እደሰታለሁ።

5 መቄዶንያ በደረስን ጊዜ እንኳ ከብዙ አቅጣጫ ችግር ደረሰብን እንጂ ምንም ዕረፍት አላገኘንም፤ በውጭ ጠብ በውስጥም ፍርሀት ነበረብን።

6 ነገር ግን የተዋረዱትን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን።

7 የተጽናናነውም በእርሱ መምጣት ብቻ ሳይሆን እናንተ እርሱን ያጽናናችሁት መሆኑን በመስማታችንም ጭምር ነው፤ ስለ እኔ ያላችሁን ናፍቆትና ሐዘን ጭንቀትም በነገረን ጊዜ ይበልጥ ደስ አለኝ።

8 ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁ መልእክት ያሳዘናችሁ ቢሆንም እንኳ መልእክቱን በመጻፌ አልጸጸትም፤ ተጸጽቼም ብሆን እንኳ የተጸጸትኩት መልእክቴ ለጥቂት ጊዜ ስላሳዘናችሁ ነው።

9 አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ የተደሰትኩበትም ምክንያት እናንተን ስላሳዘንኳችሁ ሳይሆን በሐዘናችሁ ምክንያት ንስሓ ገብታችሁ በመለወጣችሁ ነው፤ እንግዲህ ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ እኛ ምንም አልበደልናችሁም ማለት ነው።

10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ሐዘን ወደ መዳን የሚመራ በንስሓ የሚገኘውን ለውጥ ስለሚያስገኝ ጸጸትን አያስከትልም፤ ዓለማዊ ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል።

11 ይህ ሐዘናችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እንዴት ያለ የመከላከያ መልስ መስጠትን፥ እንዴት ያለ ቶሎ መቈጣትን፥ እንዴት ያለ ፍርሀትን፥ እንዴት ያለ ናፍቆትን፥ እንዴት ያለ ቅናትን፥ እንዴት ያለ ቅጣትንም እንዳስከተለ ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ደግሞ በሁሉም ነገር ከጉዳዩ ነጻ መሆናችሁን አስመስክራችኋል።

12 ስለዚህ ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍ እኔ የጻፍኩላችሁ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእግዚአብሔር ፊት ለእናንተ ግልጥ እንዲሆን ብዬ ነው እንጂ በደል ስለ ሠራውና በደል ስለ ተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም።

13 ከመጽናናታችንም በላይ ቲቶ ባገኘው ደስታ ይበልጥ ተደስተናል፤ የተደሰትነውም ሁላችሁም ቲቶን ስላጽናናችሁትና መንፈሱንም ስላሳረፋችሁት ነው።

14 በእናንተ የነበረኝን ትምክሕት ለቲቶ ነግሬው ነበር፤ እናንተም አላሳፈራችሁኝም፤ ሁልጊዜ እውነትን እንነግራችሁ ነበር፤ ይህም ስለ እናንተ ለቲቶ የነገርነው ትምክሕት እውነት በመሆኑ ተረጋግጦአል።

15 ሁላችሁም ታዛዦች እንደ ሆናችሁና በፍርሃትና በመንቀጥቀጥም እንደ ተቀበላችሁት ቲቶ ሲያስታውስ፥ ለእናንተ ያለው ፍቅር በጣም ታላቅ ሆኖአል።

16 እኔም በሁሉ መንገድ በእናንተ ለመተማመን በመቻሌ ይበልጥ ደስ ብሎኛል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos