ኢዩኤል 3:17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እስራኤል ሆይ! በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ የባዕድ ወታደሮች አይወሩአትም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ከዚያም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር፣ በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤ ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወርሯትም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “እኔም በተቀደሰ ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። |
“እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በዛሬው ምሽት ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ምግብ የሚሆናችሁን ሥጋ ታገኛላችሁ፤ በማለዳም የምትፈልጉትን ያኽል እንጀራ ታገኛላችሁ፤ በዚያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።’ ”
በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ምንም ጒዳት አይደርስም፤ ባሕር በውሃ እንደሚሞላ ምድርም እግዚአብሔርን በሚያውቁና በሚያከብሩ ሰዎች ትሞላለች።
በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤ ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤ ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም።
ጽዮን ሆይ! ተነሺ፤ ንቂ! ኀይልሽን እንደ ልብስ ልበሺ! ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ! የተዋበ ልብስሽን ልበሺ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያልተገረዙና በሥርዓት ያልነጹ ሰዎች ወደ ቅጥርሽ ውስጥ አይገቡም።
“እነርሱን ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አምጥቼ በጸሎት ቤቴም ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ፤ በመሠዊያዬም ላይ የሚያቀርቡትን የሚቃጠልና ሌሎችን መሥዋዕቶች ሁሉ እቀበላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ቤቴ የሕዝቦች ሁሉ ጸሎት ቤት ተብሎ ስለሚጠራ ነው።”
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ።
በድንና ዐመድ የሚጣልበት መላው ሸለቆ በምሥራቅ በኩል እስከ ፈረስ በር ድረስ እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከተማይቱም እንደገና ከቶ አትፈርስም፤ አትደመሰስምም።”
ነገር ግን እኔ ልዑል እግዚአብሔር በሀገሪቱ ውስጥ በቅዱሱ ተራራዬ ላይ እስራኤላውያን በሙሉ ያመልኩኛል እላለሁ፤ እዚያ እቀበላቸዋለሁ፤ እንዲሁም በዚያ ምርጥ መባዎችንና የተቀደሱ ዕቃዎች ስጦታዎችን ከእናንተ እጠባበቃለሁ።
ጅማትና ሥጋ በመስጠት ቆዳ አለብሳችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አስገብቼ እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”
ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሊታዘዙኝ ፈቃደኞች ያልሆኑት ያልተገረዙ ባዕዳን ሁሉ፥ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚኖሩት እንኳ ቢሆኑ ወደተቀደሰው ስፍራዬ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።”
በአራቱም አቅጣጫ ያሉት የከተማይቱ የቅጽር ግንቦች ጠቅላላ ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ከአሁን በኋላ የከተማይቱ መጠሪያ ስም “እግዚአብሔር በዚያ አለ!” የሚል ይሆናል።
በባሕሩና ቤተ መቅደሱ በተሠራበት ውብ ኮረብታ መካከል ባለው ስፍራ ታላላቅ ንጉሣዊ ድንኳኖችን ይተክላል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ በመጨረሻው ራሱ ይጠፋል፤ የሚረዳውም አያገኝም።”
ጌታ ሆይ! ስለ ፈጸምካቸው የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ብለህ ከተቀደሰችው ተራራህ ከኢየሩሳሌም ቊጣህንና መዓትህን እንድታነሣ እንለምንሃለን፤ በኃጢአታችንና በአባቶቻችንም በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በጐረቤቶቻችን ሁሉ መካከል ተዋርደዋል።
ሕዝቤ ሆይ! እኔ በመካከላችሁ እንዳለሁ፥ አምላካችሁም እኔ ብቻ እንደ ሆንኩና ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ኀፍረት አይደርስባቸውም።”
አንካሶች ተርፈው እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ተጥለው የነበሩትን ብርቱ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔም በጽዮን ተራራ ላይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በእነርሱ ላይ እነግሣለሁ።”
እነሆ መልካም ዜናን የሚያበሥር፥ ሰላምንም የሚያውጅ መልእክተኛ በተራሮች ላይ እየመጣ ነው። የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ክፉዎች ጠላቶችህ ፈጽሞ ስለ ተደመሰሱ ከእንግዲህ ወዲህ አገርህን ከቶ አይወሩአትም! ስለዚህ ዓመት በዓሎችህን በደስታ አክብር! ስእለትህንም ለእግዚአብሔር ስጥ!
እኔ እንድኖርባት ወደ ተቀደሰችው ከተማዬ ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ የታመነች ከተማ በመሆን ትታወቃለች፤ እኔ የሠራዊት አምላክ የምኖርበት ተራራ፥ የተቀደሰ ተራራ ተብሎ ይጠራል፤
ጸያፍ የሆነ ነገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ርኲሰትን የሚያደርግና ውሸት የሚናገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ወደ እርስዋ የሚገቡ ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ብቻ ናቸው።